ቀጥታ፡

ዜጎች ቤቶችን በቀላሉ እንዲገዙ ከባንኮች እና ከፋይናንስ ፈንድ አደረጃጀቶች ጋር በመቀናጀት እየኖሩባቸው የሚከፍሉበት ሥርዓት እየተመቻቸ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ህዳር 4/2019 (ኢዜአ)፦ ዜጎች ቤቶችን በቀላሉ እንዲገዙ ከባንኮች እና ከፋይናንስ ፈንድ አደረጃጀቶች ጋር በመቀናጀት እየኖሩባቸው የሚከፍሉበት ሥርዓት እየተመቻቸ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳመለከቱት፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ 1.5 ሚሊየን ቤቶችን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የኮንስትራክሽን ማቴሪያሎችን ማለትም ብረት፣ መስታወት እና ሴራሚክ በሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን ማሳደግ ላይ ሰፊ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ይገኛል።

ቤቶችን በመገንባት ሂደት የፋይናንስ ስኪም እና የሞርጌጅ አገልግሎት አብሮ ካልተዘረጋ ዜጎች ቤቶችን በቀላሉ መግዛት እንደማይችሉ ገልጸዋል።

ከባንኮች እና ከፋይናንስ ፈንድ አደረጃጀቶች ጋር በቅንጅት በመሥራት ዜጎች እየኖሩባቸው የሚከፍሉበት ሥርዓት እየተመቻቸ መሆኑን አመልክተዋል።

በመንግስትና በግል አጋርነት በአዲስ አበባ ውስጥ ብቻ ከመቶ ሺህ በላይ ቤቶች ተጀምረው ከአመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በጥሩ ሁኔታ መጠናቀቃቸውን ጠቁመዋል።

በተለይም እንደ መርካቶ ቅጠል ተራ ባሉ አካባቢዎች የታየው ፈጣን የቤት ግንባታና የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተገኘ ትልቅ ውጤት ሲሆን፣ መቶ ሺህ ቤቶች ተጠናቀው ሲያልቁም ይህንኑ ተሞክሮ በስፋት የማስቀጠል ሥራ እንደሚከናወን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ በገጠር የአርሶ አደሮችን የመኖሪያ ሁኔታ ለመለወጥ እንዲሁም በከተሞች መሠረታዊ አገልግሎቶችን ሳያገኙ የሚኖሩ ዜጎችን ችግር ለመቅረፍ ሚሊየን ቤቶች እንደሚያስፈልጉም ነው የገለጹት።

ይህንን ሰፊ ክፍተት ለመሙላት ገንዘብ ብቻ ሳይሆን እውቀት፣ ጥራት ያለው ዲዛይን እና ዘላቂነት ያለው ግንባታ ስለሚያስፈልግ፣ ሥራውን በፍጥነትና በጥራት ለመፈጸም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትብብር እንዲሠሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም