ምሽት አድማቂው - ጬሞ - ኢዜአ አማርኛ
ምሽት አድማቂው - ጬሞ
ምሽት አድማቂው - ጬሞምሽት አድማቂው - ጬሞ
(በቀደሰ ተክሌ - ኢዜአ ሚዛን አማን ቅርንጫፍ)
ሰው ጥበቡ ዘርፈ ብዙ፤ አበላሉ፣ አጋጌጡና አለባበሱ ሁሉ የራሱ የሆነ ልዩ የጥበብ ቀለምና ውበት ያለው ነው። ፋብሪካ ከመፈጠሩ፤ ሳይንስም ከመስፋፋቱ በፊት የሰው ልጅ በራሱ መላ ምግቡን ከሽኖ ይመገብ ነበር።
ያ ከጥንት ጀምሮ የሚጠቀምበት ባህላዊ የአመጋገብና ምግብ ዝግጅት ሥርዓት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ መስፋፋት ምክንያት ወደ ፋብሪካ ውጤቶች እየተቀየረ ቢመጣም ጨርሶ ግን አልጠፋም።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የሚገኙት ቤንቾች ተፈጥሯዊ ይዘትን የጠበቁ ባህላዊ ምግቦችን በማዘጋጀት ይታወቃሉ። አረንጓዴው ምድራቸው ያበቀላቸው ስራስሮች ከቺ ጎደሬና ሌሎችም በብዛት ለምግብነት የሚገለገሏቸው ናቸው።
ከበቆሎ ፍሬ በእጅ ተደቆሱ የሚዘጋጀው "ዳንጋላ" ፣ ኪጆና መሰል ምግቦችም በባህላዊ መንገድ ተዘጋጅተው ሲቀርቡ "ጬሞ" በተሰኘ ትኩስ መጠጥ ይታጀባሉ።
በቤንቾች ቀዬ የሚገኘው የተፈጥሮ ቡና ተክል ፍሬው ተለቅሞ ለማዕከላዊ ገበያ ከመቅረብ አልያም ለአካባቢ ፍጆታ ከመዋል ያለፈ ትርጉም አለው።
የቤንች እናቶች ቅጠሉን በወጉ ሰብስበው በሸክላ ምጣድ ክሽ አድርገው በማድረቅ ለሌላ አገልግሎት ያዘጋጃሉ። የደረቀውን የቡና ቅጠል አድቅቀው በማፍላት የዶሮ ዓይን የመሰለ ቡና ወይም በእነሱ አጠራር "ጬሞ"ን ያዘጋጃሉ።
የቡና ቅጠል ቡና ውይም ጬሞን ለየት የሚያደርገው በብዙ የጓሮ ቅመማ ቅመሞች ታጅቦ መዘጋጀቱ ነው። ለአብነትም ነጭ ሽንኩርት፣ በሶብላ፣ ድምብላል፣ ኮሰረት፣ ጤናአዳም፣ ኮረሪማ፣ ሚጥሚጣ ወይም ደቆ የመሳሰሉት ጬሞን ጬሞ ከሚያሰኙ ግብአቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
እነዚህ የጬሞ ግብአቶች በማሽን የተፈጩ አልያም እሴት ተጨምሮባቸው የተቀመሙ የፋብሪካ ውጤቶች አይደሉም። ከራሳቸው ጓሮ ተክለው ጬሞን ሲያፈሉ እለቱን ቀንጥሰው በትኩሱ የሚጨምሯቸው እንጂ።
ይህ መሆኑ ደግሞ ከጬሞው ተፈጥሯዊ ጣዕምና የንጥረ ነገር ይዘቶችን በቀጥታ ለማግኘት የሚያስችል ዕድልን ይፈጥራል። ከዚህ የተነሳ ጬሞ እንደ ትኩስ መጠጥ ከማገልገል ያለፈ ጥቅም ያለው ሆኖ ተገኝቷል። ለጉንፋን፣ ደረቅ ሳል፣ ብርድና መሰል ሕመሞች ሁነኛ ባህላዊ መድኃኒት ተደርጎ ይወሰዳል።
ይህ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው ጬሞ በቤንቾች ምድር ይዘወተራል። እንግዳ ቢመጣ ከእርጎና ኪዥ (አይብ)፣ ከጎደሬ፣ ከቺናና ሌሎች ከበቆሎ ከሚዘጋጁ ምግቦች ጋር ጬሞ አብሮ ይቀርባል።
ለአራሹ አባወራ ወደ እርሻ ቦታ ለመያዝ በሚያመች እቃ ተወስዶለት ይጠጣል። ለሐዘንና ደስታ፣ ለደቦና መሰል ሰዎች በኅብረት በሚሰበሰቡባቸው ስፍራዎችም ጬሞን አፍልቶ ማቅረብ በቤንቾች ባህል የተለመደ ነው። ይህ ሥርዓት ከገጠር ተሻገሮ በከተማም እየተለመደ መምጣቱ ደግሞ ይበል የሚያሰኝ ነው።
ጬሞ በሚዛን አማን ከተማ ውስጥ የፈጠረው የምሽት ትዕይንት ደግሞ ለየት ያለ ነው። መሸት ሲል ቀን በጫማ መጥረግ ሥራና ሌሎች አገልግሎቶች ተይዘው የዋሉ የጎዳና ዳር ቦታዎች ከ12 ሰዓት በኋላ ተራውን ጬሞ ለሚያፈሉ እንስቶች ይለቃሉ።
ከጬሞ ባሻገር ንፍሮ፣ ጎደሬ፣ ከቺ እና ሌሎች የስራስር ምግቦች ተዘጋጅተው ወደ አደባባይ ይወጣሉ። ቀን በተለያዩ ሥራዎች የዋለ ሰው ወደ ቤት ከመግባቱ በፊት በከተማዋ ከጫፍ እስከ ጫፍ ከተዘጋጇ የጬሞ ቦታዎች አንዱ ላይ አረፍ ይላል።
የሚዛን አማን ጎዳና ኮሪደሮች የምሽት ድባብ የሚደምቀው በጬሞ ነው። ጓደኛ ሲገናኝ ጬሞ ልጋብዝህ የሚባባልበት፣ ጬሞ ቦታ እንገናኝ ተብሎ የሚቀጠርበት መገናኛ፣ ወግ መጫወቻና ጊዜ ማሳለፊያ ምቹና ተመራጭ ስፍራም እየሆነ መጥቷል።
ከጬሞ ጋር አብረው የሚቀርቡ ባህላዊ ምግቦች መኖራቸው ደግሞ ለከተማዋ ነዋሪ ትልቅ ጥቅም ይሰጣል። ድሃው በአነስተኛ ዋጋ ጬሞና ንፍሮ በልቶ ጠግቦ የሚያድርበትን ምቹ ዕድል መፍጠር የቻለ ተግባር ነው ማለት ይቻላል።
እንደዚህ አይነት ሀገር በቀል ምርቶች ላይ የተመረኮዘ የአመጋገብ ሥርዓት ለጤና ጠቃሚ በኢኮኖሚም ትርጉም ያለው በመሆኑ አደባባይ አውጥቶ የመጠቀሙ ባህል ሊጠናከር ይገባል እንላለን። ሰላም!