የሕዝባችንን የቤት ጫና ማቃለል ለእኛ የልማት ግብ ብቻ ሳይሆን አደራና ኃላፊነት ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
የሕዝባችንን የቤት ጫና ማቃለል ለእኛ የልማት ግብ ብቻ ሳይሆን አደራና ኃላፊነት ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 4/2019 (ኢዜአ)፦ የሕዝባችንን የቤት ጫና ማቃለል ለእኛ የልማት ግብ ብቻ ሳይሆን አደራና ኃላፊነት ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባዋ ቃል በተግባር በሚል ርዕስ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት እንዳመለከቱት፣ ከጉባ ብስራቶች አንዱ በሆነውና እንደ ሀገር በአምስት ዓመታት ውስጥ 1.5 ሚሊዮን ቤቶችን ለዜጎች ለማስረከብ በተገባው ቃል መሠረት በአዲስ አበባም ሰፊ የግንባታ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በከተማዋ በ21 ሳይቶች እየተገነቡ ካሉት 100 ሺህ ቤቶች ውስጥ 50 ሺህ የሚሆኑት በከተማ አስተዳደሩ በጀት፣ ቀሪዎቹ 50 ሺህ ቤቶች ደግሞ በመንግሥትና በግል አጋርነት እንዲሁም በቤት ሥራ ማኅበራት አማካኝነት ግንባታቸው እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር በመሆን በቱሉ ዲምቱ እየተገነቡ የሚገኙ 33 ብሎኮችን እና በአዲስ ከተማ ቅጠል ተራ የሚገኙ 9 ብሎኮችን መጎብኘታቸውን ገልጸው፣ የግንባታዎቹ ሂደት በጥሩ አፈፃፀም ላይ እንደሚገኝ መመልከታቸውን አስታውቀዋል።
የሕዝባችንን የቤት ጫና ማቃለል ለእኛ የልማት ግብ ብቻ ሳይሆን አደራና ኃላፊነት ነው ያሉት ከንቲባዋ፣ ይህንን ለመወጣት በቀን 24 ሰዓት በሳምንት 7 ቀን (24/7) ተግተው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።