ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ለማስተናገድ በዝግጅት ላይ የምትገኘው ጅማ

ጅማ፤ ኅዳር 4/2019 (ኢዜአ)፦ 21ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ለማስተናገድ በዝግጅት ላይ የምትገኘው ጅማ፣ በሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት አማካኝነት ገጽታዋን ከማሳመር ባሻገር ሰፊ የሥራ ዕድል እየፈጠረች መሆኑን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ።

የዘንድሮውን 21ኛውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የኦሮሚያ ክልል በታሪካዊቷና የንግድ ማዕከል በሆነችው ጅማ ከተማ እንዲያስተናግድ መመረጡን ተከትሎ፣ ከተማዋ እንግዶቿን በተሟላ መሠረተ ልማትና ውብ ገጽታ ለመቀበል ሰፊ ዝግጅት ስታደርግ ቆይታለች።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተሞችን ዘመናዊ፣ ጽዱና ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ኢንሼቲቭ አካል የሆነው የጅማ ከተማ የኮሪደር ልማት፣ የመጀመሪያውን ምዕራፍ በስኬት አጠናቅቆ በአሁኑ ወቅት ሁለተኛውን ምዕራፍ የመጨረሻ ሥራዎች ላይ ይገኛል። 

ይህ ልማት የከተማዋን የትራፊክ ፍሰት ከማቀላጠፍና ገጽታዋን ከመቀየር ባለፈ፣ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠርና የአካባቢውን የንግድ እንቅስቃሴ በማነቃቃት የከተማዋን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እያፋጠነ ይገኛል።

የከተማዋ ነዋሪዎች የኮሪደር ልማቱ በጥራትና በፍጥነት እየተከናወነ መሆኑ እንዳስደሰታቸው ገልጸው፣ ልማቱ ከተማዋ ለብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን አከባበር የተሻለ ገጽታ ይዛ እንድትቀርብ ከማስቻሉም በላይ በኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዘርፎች እያመጣ ያለውን ለውጥ አድንቀዋል።

አቶ ሚሊዮን ዘለቀ፤ የኮሪደር ልማቱ የጅማ ከተማን ገጽታ እያሻሻለና ይበልጥ ማራኪ እያደረጋት መሆኑን ገልጸዋል። 

በተለይም በሁለተኛው ምዕራፍ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች የከተማዋን ውበት ከማሳደግ ባሻገር የንግድ ማዕከላት እንዲስፋፉና የከተማዋ እንቅስቃሴ እንዲጎለብት እያገዘ መሆኑን አስረድተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የኮሪደር ልማቱ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ጠቅሰው፣ የልማቱ ውጤት ለከተማዋ ነዋሪዎች የተሻለ የኑሮና የእንቅስቃሴ አካባቢ እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

ሌላኛዉ የከተማዋ ነዋሪ ወጣት ነዚፍ ቢያ በበኩሉ፣ የኮሪደር ልማቱ ለበርካቶች ሰፊ የስራ ዕድል መፍጠሩን ተናግሯል።

አሁን ላይ በልማቱ ምክንያት የሥራ ዕድል አግኝቶ በመሥራት የቤተሰቡን ወጪ እየሸፈነ መሆኑንም ገልጿል።

ልማቱ ከከተማ ውበትና መሠረተ ልማት ግንባታ ባሻገር በዜጎች የኑሮ ሁኔታ ላይ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ያለውን አቅም የሚያሳይ መሆኑን አመልክቷል።

ሌላኛው ነዋሪ አቶ አህመድ ቡሹራ በበኩላቸው፣ በንግድ ሥራ የተሰማሩ እንደመሆናቸው የኮሪደር ልማቱ ለንግዳቸው መስፋፋት የተሻለ ዕድል እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል። 

የከተማዋ ገጽታ መሻሻልና የንግድ ማዕከላት መስፋፋት ለንግድ እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ መሆኑንም አስረድተዋል።

በተጨማሪም የኮሪደር ልማቱ በጥራትና በፍጥነት እየተከናወነ መሆኑ እንዳስደሰታቸው ጠቅሰው፣ ሥራው በታቀደለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ እየተደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል።

የጅማ ከተማ ከዓመታት በኋላ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እየለማች እና እየተዋበች መሆኑ እንዳስደሰታቸው የተናገሩት ደሞ አቶ ደመላሽ ዘውዴ ናቸዉ።

የጅማ ከተማ የኮሪደር ልማት የመጀመሪያ ምዕራፍ መጠናቀቁን ተከትሎ፣ ሁለተኛውን ምዕራፍ በመጪው ህዳር 29 ቀን በጅማ ከተማ ለሚከበረው 21ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች  ቀን አከባበር ዝግጁ ለማድረግ የማጠናቀቂያ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።

ነዋሪዎቿም የኮሪደር ልማቱ ለበዓሉ ተሳታፊዎችና እንግዶች የተሻለ የከተማ ገጽታ ለማቅረብ ከማገዙም በላይ፣ ከበዓሉ በኋላም ለከተማዋ ነዋሪዎች የሚጠቅም ዘላቂ የልማት ውጤት ይሆናል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም