አረንጓዴ ዐሻራ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎችን ለመከላከል ለምታደረገው ጥረት ዋና ማሳያ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አረንጓዴ ዐሻራ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎችን ለመከላከል ለምታደረገው ጥረት ዋና ማሳያ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 4/2019 (ኢዜአ)፦ አረንጓዴ ዐሻራ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎችን ለመከላከል ለምታደረገው ጥረት ትልቅ ማሳያ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ገለጹ።
31ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 31) በቱርኪዬ አንታሊያ እየተካሄደ ይገኛል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በCOP 31 ላይ ስላከናወኗቸው ጉልህና ዘርፈ ብዙ ተግባራት፣ እንዲሁም ሀገሪቱ ኮፕ 32ን ለማስተናገድ እያደረገች ስላለው ቅድመ ዝግጅትና በዚህ ሂደት ስለሚከናወነው ብሔራዊ ገጽታ ግንባታ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ቢልለኔ ስዩም እንደገለጹት፣ በአረንጓዴ ዐሻራ ባለፉት ስምንት ዓመታት ውስጥ ከ56 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን ገልጸዋል።
አረንጓዴ ዐሻራ ኢትዮጵያ ዓለምን ካሳሰበው የአየር ንብረት ለውጥ ችግር ለመከላከል የምታደርገው ጥረት ዋና ማሳያ እና ትልቅ የተስፋ ሂደት መሆኑን አመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ከመትከል ባለፈ ዘላቂ ክብካቤ ማድረግን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ባህል ሊሆን እንደሚገባ ደጋግመው ማንሳታቸውን ጠቅሰዋል።
ከንጹህ ኢነርጂ ጋር በተገናኘም የሶላር፣ የንፋስ እና የሃይድሮ ፓወር አማራጮችን በመጠቀም ኢነርጂን ልማቶች ለሀገር ውስጥ እና ሌሎች ሀገራት ገበያ በማቅረብ ረገድ ትልቅ አቅም እየተገነባ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ሀገሪቱ ያላትን የንፁህ ኢነርጂ አቅም በሰፊው ለመጠቀም የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል።
የነፋስ እና የሶላር ሃየል ማመንጫዎች የዚሁ ማሳያ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለሀገሪቱ የኢነርጂ እድገት አቅም ማደግ ትልቅ ሚና ያለው ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ይህንን ታሪካዊ ፕሮጀክት በጉባኤው በተዘጋጀው የኢትዮጵያ ፓቪሊዮን ላይ በሰፊው እንደሚያስተዋውቅ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እየሠራችባቸው የሚገኙት የንፁህ ሃይል ልማቶች አጠቃላይ የአካባቢ ጥበቃን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን፣ በዓለም ደረጃ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ጉዳዮች እንደሆኑም አመልክተዋል።