ቀጥታ፡

በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ኢትዮጵያ ከሞዛምቢክ ጋር ትጫወታለች

አዲስ አበባ፤ ህዳር 4/2019 (ኢዜአ)፦ በ36ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የምድብ 10 ሶስተኛ ጨዋታውን ዛሬ ከሞዛምቢክ ጋር ያደርጋል።

የሁለቱ ሀገራት ጨዋታ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በዚምፔቶ ስታዲየም ይካሄዳል።

በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምድቡ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግዶ ያለ ምንም ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል።

አሰልጣኝ ዮሐንስ ለጨዋታው ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ ያደረጉ ሲሆን ብሔራዊ ቡድኑ ላለፉት ሁለት ሳምንታት ልምምዱን ሲያደርግ ቆይቷል።


በ60 ዓመቱ የሀገሯ ዜጋ ቺኩኒዮ ኮንዴ የሚመራው የሞዛምቢክ ብሔራዊ ቡድን ለ26 ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ ዝግጅቱን አከናውኗል።

ከጥቅምት 30 2019 ዓ.ም አንስቶ በማፑቶ በመሰባሰብ ልምምዱን ሲያደርግ ቆይቷል።ተጋጣሚው ሞዛምቢክ በአራት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።

ሁለቱ ሀገራት ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ ተገናኝተው ያውቃሉ።

እ.አ.አ በ2023 በአልጄሪያ አስተናጋጅነት በተካሄደው የአፍሪካ ሀገራት እግር ኳስ ሻምፒዮና (ቻን) ባደረጉት ጨዋታ ያለ ግብ አቻ ተለያየተዋል።

ሀገራቱ እ.አ.አ በ1980 በአዲስ አበባ ስታዲየም ባደረጉት የወዳጅነት ጨዋታ ኢትዮጵያ 3 ለ 2 አሸንፋለች።

ብሔራዊ ቡድኑ የመጨረሻ ልምምዱን ሐሙስ ዕለት አከናውኗል።

የቡድኑ ስብስብ በጥሩ ሞራል እና ጤንነት ላይ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሞዛምቢክ ጋር ሁለተኛ ጨዋታዋን ህዳር 8 2019 ዓ.ም ያደርጋል።

በተያያዘም የምድቡ መሪ ሴኔጋል ትናንት ማምሻውን ከሱዳን ጋር ባደረገችው ጨዋታ 4 ለ 1 በማሸነፍ ነጥቧን ወደ ሰባት ከፍ አድርጋለች።

ሱዳን በሶስት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዛለች። 36ኛው የአፍሪካ ዋንጫ እ.አ.አ በ2027 በኬንያ፣ ዩጋንዳ እና ታንዛንያ ጣምራ አዘጋጅነት ይካሄዳል።

አህጉራዊው ውድድር ከሰኔ 12 እስከ ሐምሌ 10 ቀን 2019 ዓ.ም በሶስቱ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በሚገኙ ሰባት ስታዲየሞች ይደረጋል። በውድድሩ ላይ 24 ሀገራት ይሳተፋሉ።

ቀሪ ወደ አፍሪካ ዋንጫው የሚያልፉ 21 ሀገራት በማጣሪያ ጨዋታዎች ይለያሉ። በዚህም 48 ሀገራት በ12 ምድቦች ተከፍለው ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም