ቀጥታ፡

የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በምክክር ሀገር ለማፅናትና ሥልጡን ሀገር ለመገንባት ቁልፍ ሚና አለው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 4/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የብዝሃነት ጸጋ መጠቀም በምክክር ሀገር ለማፅናትና ሥልጡን ሀገር ለመገንባት ቁልፍ ሚና እንዳለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሙፈሪሃት ካሚል 21ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል አከባበርን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን ማብራሪያ ሰጥተዋል።

21ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን "በብዝሃነት የደመቀች በምክክር የፀናች ሥልጡን ኢትዮጵያ" በሚል መሪ ሀሳብ በኦሮሚያ ክልል ጅማ ከተማ ይከበራል።

የዘንድሮው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ለአምስት ቀናት የሚከበር ሲሆን፤ ሕዳር 21 የወንድማማችነት ቀን፣ 26 የአብሮነት፣ 27 በዓሉን ለሚያስተናግዱ ክልሎች የሚሰጥ በመሆኑ የዘንድሮው የኦሮሚያ ቀን፣ 28 የምክክር ቀን እንዲሁም ሕዳር 29 የኢትዮጵያ ቀን ተብሎ ተሰይሟል።

የዘንድሮው መሪ ሀሳብ የጋራ ቃል ኪዳን፣ የጋራ ዕቅድና የጋራ ግንዛቤ በመፍጠር፤ ብዝሀነት ሀብት፣ ምክክር የሥልጣኔ መንገድ፣ ሥልጡን ማህበረሰብን ደግሞ የግቡ መዳረሻ ያደረገ ነው።

አፈ ጉባኤ ሙፈሪሃት ካሚል በመግለጫቸው፤ ሁለንተናዊ ሉዓላዊነቷን ያረጋገጠች አምራች፣ መሪ እና ሥልጡን ኢትዮጵያን እውን ማድረግ የሚያስችል የ25 ዓመት የትውልድ ፍኖት ተቀርጿል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተሳለጠ የፌዴራል ሥርዓት በመፍጠር ረገድ አይተኬ ሚና እንዳላቸው ገልጸው፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚጋራው ርዕይ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የብዝሃ ማንነት ሀገር ናት ሲባል በብዙ ማንነቶች የደመቀች ማለታችን ነው ያሉት አፈ ጉባኤዋ፤ ብዝሃነት በአግባቡ መመራት ከቻለ ለፈጠራ፣ ልህቀትና ሀገራዊ ሽግግር ወሳኝ ሀብት መሆኑን ገልጸዋል።

ስለሆነም ኢትዮጵያውያን የብዝሃነት ጸጋችንን በመንከባከብና ለልማት በማዋል ለዕድገታችን ምንጭ ልናደርገው ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የብዝሃነት ሀብታችንን ለመጠቀም እርስ በርስ የምንተዋወቅበት መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።

የ2019 በጀት ዓመት ኢትዮጵያውያን በድምፃቸው ይበጀናል ብለው የመረጡት መንግሥት የተመሰረተበት ወቅት መሆኑን በማንሳት፤ የኢትዮጵያን የረጅም ጊዜ የልማት ትልም ለመሥራት ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።

21ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የመንግሥት የልማት ተልዕኮዎች በሚያሳካ መንገድ ለማክበር ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

ስለሆነም ቀኑ በዓልን ከማክበር ባሻገር ትልቅ ሀገር ለማሻገርና ዘላቂ ብልፅግናን ለማረጋገጥ መሰረት ይጥላል ብለዋል።

በዓሉ "በብዝኃነት የደመቀች በምክክር የፀናች ሥልጡን ኢትዮጵያ" በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚከበር ያነሱት አፈ ጉባኤዋ፤ ኢትዮጵያ በምክክር የጸናች ሲባል አንድነቷ የተጠበቀ ምክክርን ባህሏ ያደረገች ማለት መሆኑን ገልጸዋል።

ምክክርን ባህሉ ያደረገ የተግባባ ሕዝብ ፈጣን ዕድገት፣ አሳታፊና አካታች ልማት ለማስመዝገብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ገንቢ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በሥልጡን የምክክር ባህል የተጣለውን መሰረት ወደ ላቀ ምዕራፍ የማሸጋገር ተልዕኮውን መወጣት እንዳለበት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም