ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከቱርኪዬ ፕሬዝዳንት ረጅብ ጣይብ ኤርዶጋን ጋር ያደረጉት ውይይት የሀገራቱን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የሚያስችል ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 4/2019 (ኢዜአ)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከቱርኪዬ ፕሬዝዳንት ረጅብ ጣይብ ኤርዶጋን ያደረጉት ውይይት የሀገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የሚያስችል መልካም አጋጣሚን መፍጠሩን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ገለጹ።

31ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 31) በቱርኪዬ አንታሊያ እየተካሄደ ይገኛል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኮፕ 31 ላይ ስላከናወኗቸው ጉልህና ዘርፈ ብዙ ተግባራት፣ እንዲሁም ሀገሪቱ ኮፕ 32ን ለማስተናገድ እያደረገች ስላለው ቅድመ ዝግጅትና በዚህ ሂደት ስለሚከናወነው ብሔራዊ ገጽታ ግንባታ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ፕሬስ ሴክሬተሪ ቢልለኔ ስዩም እንደገለጹት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቱርኪዬ ቆይታቸውን ከፕሬዝዳንት ረጅብ ጣይብ ኤርዶጋን ጋር በሁለትዮሽ ውይይት መጀመራቸውን አውስተዋል።

ኢትዮጵያ እና ቱርኪዬ በዲፕሎማሲ፣ በኢኮኖሚ እና በተለያዩ መስኮች ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ የትብብርና የትስስር ታሪክ እንዳላቸው ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቱርኪዬ ሰራ ጉብኝቶችን ማድረጋቸውንና በተለያዩ ስብስባዎች ላይ መሳተፋቸውን አመልክተዋል።

ባለፈው ዓመት የቱርኪዬ ፕሬዝዳንት ረጅብ ጣይብ ኤርዶጋን ወደ ኢትዮጵያ ከከፍተኛ ልዑካን ቡድን ጋር በመምጣት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ውይይቶች መደረጋቸውንም አንስትዋል።

በቱርኪዬ አንታሊያ የተደረገው የሁለትዮሽ ውይይት ከዚህ በፊት የተነጋገሩባቸውን ጉዳዮች የደረሱበትን ደረጃ ለመፈተሽ ጥሩ አጋጣሚ እንደነበር አመልክተዋል።

ከዚህ ባለፈም ኢትዮጵያ በሚቀጥለው ዓመት የምታስተናግደውን ኮፕ 32 አስመልክቶ ከቱርኪዬ ምን መማር እና ምን ድጋፎች ማግኘት እንደሚቻል ሰፊ ውይይት መደረጉን ጠቁመዋል።

ቱርኪዬ ለኢትዮጵያ የኮፕ 32 ዝግጅት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነች ማረጋገጧን ጠቅሰዋል።

የቱርክ ወገኖች በጉባኤው ዝግጅት ዙሪያ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ክብር በመስጠት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ በቁርጠኝነት መግለጻቸውን ፕሬስ ሴክሬተሪዋ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም