ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ዕውቀት መር የማህበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችን አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ዕውቀት መር የማህበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችን አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል አስታወቀ
ጋምቤላ፤ ሕዳር 3/2019( ኢዜአ) ፦ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ዕውቀት መር የማህበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ልዩ ትኩረት መስጠቱን አስታወቀ።
ዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ተኮር የሆኑ የልማት ሥራዎችን ከአጋር አካላት ጋር ተባብሮ ለመስራት የሚያስችል የውይይት መድረክ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ አካሂዷል።
በመድረኩ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ድሪባ ኢትቻ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ዩኒቨርሲቲው ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ ዕውቀት መር የማህበረሰብ አገልግሎትን ለማጠናከር እየሰራ ይገኛል።
በዚህም የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉና ችግር ፈቺ የሆኑ ምርምሮችን ከማስፋት አኳያ ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ነው የገለጹት።
በተለይ በግብርና፣ በማዕድን፣ በቱሪዝምና በሰላም ግንባታ ዘርፎች የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ የአጋር አካላት ተሳትፎ ይበልጥ መጠናከር እንዳለበት ገልፀዋል።
በክልሉ ያለውን የተፈጥሮ ፀጋ ተባብሮ ማልማት ከተቻለ ከአካባቢው አልፎ ለሀገር የሚተርፍ ሃብት መኖሩንም አንስተዋል።
የውይይት መድረኩ ዋና ዓላማም የማህበረሰቡን ሕይወት የሚለውጡ የልማት ሥራዎችን በጋራ አቅዶ ለመተግበር ያለመ መሆኑን አመልክተዋል።
በዩኒቨርሲቲው የምርምር ዓለም አቀፍ ግንኙነትና አጋርነት አስተባባሪ መምህር ዘላለም በፍቃዱ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ተግባሩ ባለፈ ሰው ተኮር የልማት ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ተቋሙ የጀመራቸውን የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ሥራዎች ለማጠናከር የአጋር አካላት ተሳትፎ ወሳኝ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።
በመድረኩ ላይ የተሳተፉት አጋር አካላትም፣ ዩኒቨርሲቲው በክልሉ ያሉትን የተፈጥሮ ሃብቶች በምርምርና በቴክኖሎጂ አስደግፎ ለማልማት እያከናወነ ያለው ተግባር የሚደነቁ መሆናቸውን አንስተዋል።
በመሆኑም በተቋሙ የተጀመሩ ማህበረሰብ ተኮር የልማትና የሰላም ግንባታ ሥራዎችን ለማስፋትና ለማጠናከር ተባብረው ለመስራት መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ የልማት አጋር አካላት፣ የሀይማኖት አባቶችና ሌሎች ተጋባዥ እንግድች ተገኝተዋል።