የኢትዮጵያ አረንጓዴ ማዕበል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አረንጓዴ ማዕበል
(በሙሴ መለሰ)
ኢትዮጵያ የአሸናፊዎች ሀገር ናት። ትጋት፣ አይበገሬነት እና ጽናትን የማንነት ካባቸው አድርገው የለበሱ ዜጎቿ ፊታቸው ካለው ችግር ይልቅ የነገን መጻኢ ብሩህ ተስፋ እያዩ በአንድነት በመጓዝ በስኬት ላይ ስኬት በድል ላይ ሌላ ድል በገድል ላይ አዲስ ገድል እያስመዘገቡ ኖረዋል አሁንም በዚህ ብርቱ የድል አድራጊነት መንፈስ ቀጥለዋል።
ለማሳያነት አትሌቲክስን እንመልከት። ከኢትዮጵያ የተለያዩ መልክዐ ምድሮች የፈለቁ አትሌቶች ለሀገሪቷ ድል ከማስመዝገብ ባለፈ መልካም ገጽታዋን ገንብተዋል ባንዲራዋ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ አድርገዋል ኢትዮጵያ የጀግኖች ሀገር ናት የሚለውን እሳቤ ከንግግር ባለፈ በተግባር አሳይተዋል።
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከድላቸው ጀርባ አንድ ትልቅ ኃይል አለ እሱም የቡድን ስራ ይባላል። አትሌቶች ከግል ክብራቸው ይልቅ ሀገርን በማስቀደም በቡድን ስራ የሚያስመዘግቡት ድል “ አረንጓዴው ጎርፍ” (Green Wave) የሚል ታዋቂ ስያሜ አሰጥቷቸዋል። አረንጓዴ ጎርፍ ኢትዮጵያውያንን በደስታ ጮቤ አስረግጧል ። ይህ የአረንጓዴ ማዕበል መንፈስ ከአትሌቲክስ መሮጫ መም እና ሜዳ ወደ ደኖች፣ ኮረብታዎች እና እርሻ ስፍራዎች ሰተት ብሎ ገብቷል። በአረንጓዴ አሻራ አማካኝነት።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው አረንጓዴ አሻራ ስምንተኛ ዓመቱ ላይ ደርሷል። እስከ አሁን ከ56 ቢሊዮን በላይ ችግኝ ተተክለዋል።
በዚህ አኩሪ ስራ ላይ በሚሊዮን የሚቆጥሩ ዜጎች ተሳትፈዋል። አትሌቶች በመሮጫ ስፍራው የብሄራዊ አይበገሬነት እና ክብር ምልክት ሲሆኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በነቂስ ወጥተው ችግኝ በመትከል የደን መልሶ ልማት እና የአካባቢ ጥበቃ ስራ አሸናፊ ሆነዋል። ሚሊዮኖች ችግኝ ሲተክሉ ልክ እንደ አትሌቶቹ አንድነት፣ ጽናት እና አላማን በቁርጠኝነት ማሳካትን አሳይተዋል።
ኢትዮጵያውያን ያሳዩት አንድነት እና ህብረት ዓለምን አስደንቋል። ለመሆኑ ኢትዮጵያውያን ለምን በነቂስ ወጥተው ችግኝ ይተክላሉ? ለሚለው ጥያቄ ከፊት ለፊት የሚመጣው ምላሽ ችግኝ መትከል ለከባቢ አየር ጥብቃ አንገብጋቢ አጀንዳ ከዛ ሲያልፍም የማህበራዊ እና የኢኮኖሚ ፈተናዎችን ለመፍታት ቁልፍ መፍትሔ እንደሆነ በጽኑ ስለሚያምኑ ነው።
አረንጓዴ አሻራ በርካታ ትሩፋቶች እና በረከቶች ያሉት ነው። የኦክስጅን አቅርቦት ጨምሯል፣ የአየር ንብረት ሚዛንን ጠብቋል አልፎም የተራቆተ መሬት መልሶ ወደ ነበረበት እንዲመለስ እያደረገ ይገኛል። ደኖች የአፈር ለምነትን በማሻሻል እና ውሃን አቅቦ በመያዝ የምግብ ምርታማነትን እንዲያድግ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።
ከዚህ አንጻር አረንጓዴ አሻራ ያለው ሚና ግዙፍ ነው። ምርታማ የሆነ መሬት ሲሰፋ እና ስነ ምህዳሮች ከጉዳታቸው አገግመው ነባር ይዞታቸውን ሲይዙ ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነነቷን የማረጋገጥ፣ አይበገሬ አረንጓዴ ኢኮኖሚ የመገንባት እና አካባቢን የመጠበቅ ህልሟ እንዲሳካ ያደርጋል።
አረንጓዴ አሻራ ከአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም የተሻገረ ትርጉም ያለው ነው የአንድነት እና የብሄራዊ ክብር መገለጫም ሆኗል። ኢትዮጵያውያን ለአንድ አላማ ከቆሙ እና ከተባበሩ ከስኬት ማማ ለመድረስ የሚያግዳቸው ነገር እንደሌለ በግልጽ አሳይቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አረንጓዴ አሻራ ኢትዮጵያ ትላልቅ ዕቅዶችን አቅዳ ህዝቧን አስተባብራ ማሳካት እንደምትችል ለዓለም ያሳየችበት ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።
በተለይም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በነቂስ ወጥተው መሳተፋቸው የሀገርን የጋራ ራዕይ ለማሳካት ያላቸውን ፍላጎት እና ቁርጠኝነት የሚያሳይ እንደሆነ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ስኬት የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ከፍታ ጨምሯል። እ.አ.አ በ2027 የሚካሄደውን 32ኛውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 32) እንድታስተናግድ መመረጧ የዚሁ ከፍታ ማሳያ ነው።
በቱርኪዬ አንታሊያ እየተካሄደ በሚገኘው 31ኛው የተበባሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ኢትዮጵያ በከፈተቸው ፓቪሊዮን የአረንጓዴ አሻራ ትሩፋቶቿን ለዓለም እያሳየች ነው።
አረንጓዴ አሻራ መንግስት እና ህዝብ እጅና ጓንት ሆነው መጻኢው ጊዜ ብሩህ የሆነና አረንጓዴ የለበሰች ሀገር ለመፍጠር ቆርጠው ከተነሱ የማይሳካ ነገር እንደሌለም አመላካች ነው።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ አማካኝነት ትላልቅ ህልሞቿን፣ እቅዶቿ እና ራዕዮቿን ማሳካት እንደምትችል በግልጽ አሳይታለች።
ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ የተግባር ምላሽ በመስጠት፣ የተፈጥሮ ጠበቃ በመሆን እና ዘላቂ ልማትን በማረጋገጥ ጉዞ ዘላቂ መሪነቷን እያሳየች ትገኛለች። ኢትዮጵያ በአፍሪካ እና በተቀረው ዓለም የአረንጓዴ ትራንስፎርሜሽን አሸናፊ እና ቁንጮ ሆና መቀጠሏ አይቀሬ ነው።
ለግዙፍ ሀገራዊ አላማ በሚሊዮኖች ደረጃ የሚተመው አረንጓዴ ማዕበልም ይህን ግብ የሚያሳካ ትልቅ ሀብት እና አቅም ሆኖ ይቀጥላል።