ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስረዳት የፎረሙ ቁልፍ ዓላማ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 3/2019 (ኢዜአ)፦የናይልና የቀይ ባህር ስትራቴጂክ ፎረም የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የሀገራችን ስትራቴጂያዊ የህልውና ጉዳይ ስለመሆኑ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማስረዳትና በጉዳዩ ላይ የፖሊሲ ተጽዕኖ ፈጣሪ የአድቮኬሲ ሥራዎችን ለማከናወን መመስረቱን ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ሰሎሞን ተፈራ ገለጹ።

በቅርቡ ህጋዊ ሰውነት የተሰጠው የናይል እና ቀይ ባህር ስትራቴጂክ ፎረም ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የፎረሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሰሎሞን ተፈራ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ፎረሙ የኢትዮጵያን ሀገራዊ ጥቅሞች በዲፕሎማሲ፣ በምርምርና በህጋዊ ዳራዎች ላይ በመመሥረት ለማስከበር ሰፊ ስራዎችን ያከናውናል።

ፎረሙ የናይል እና የቀይ ባህርን ጉዳይ በተመለከተ የኢትዮጵያን ሀገራዊ ትርጉሞች በዲፕሎማሲ መንገድ በብቃት ለማስተባበርና በመርህ ለመደገፍ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ባህር በር ጥያቄ ለኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ማስረዳት፣ የፖሊሲ አድቮኬት ስራ ማከናወን ቁልፍ ዓላማዊ መሆኑን አስታውቀዋል።

የዓባይ እና የቀይ ባህር ጉዳይ የሁሉም ዜጋ መሆኑን ግንዛቤ ለመፍጠር በትምህርት ቤቶችና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የመድረክና የግንዛቤ የማስጨበጫ ስራዎች እንደሚከናውኑ ተናግረዋል።

የሀገራችን የቀይ ባህር ተደራሽነትን በተመለከተ የታሪክ፣ የህግ፣ የጂኦፖቲካልና የኢኮኖሚ መሰረታዊ መከራከሪያዎችን በማዘጋጀት ለሀገር ውስጥና ለውጪ ማህበረሰብ የማስረዳት ስራ እንደሚሰራ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ባህር በር አልባ መሆን በሀገሪቱ ላይ የሚያስከትለውን ዘርፈ ብዙ ተጽዕኖ በምርምርና በጥናት በማሳየት ለዜጎችና ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ ግንዛቤ ይፈጥራል ብለዋል።

የዓባይ ወንዝ ለኢትዮጵያና ለቀጣናው ሀገራት የሚያበረክተውን ሁለገብ ጠቀሜታ በእውቀትና በመረጃ ላይ ተመስርቶ ለማስረዳት ጥረት እንደሚያደርግ ገልፀዋል።

በሀገር አቀፍና በቀጣናዊ ደረጃ የአካዳሚክ ውይይቶች፣ የምርምር ኮንፈረንሶች እና የፖሊሲ መድረኮች እንዲጠናከሩ ያደርጋል ነው ያሉት።

ፎረሙ ከሀገር ውስጥ እስከ አህጉር አቀፍ ያሉ የውሃ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ እና የጂኦፖቲካል ጉዳዮችን በምርምር በመደገፍ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ለማጠናከር እና የኢትዮጵያን የባህር በርና ፍላጎቶች በሰላማዊ መንገድ እውን ለማድረግ ሚናውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም