ኢትዮጵያ እና ቻይና ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸውን ለማጠናከር ት እንደሚሰሩ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ቻይና ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸውን ለማጠናከር ት እንደሚሰሩ ገለጹ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 3/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ቻይና የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን በፓርቲ ለፓርቲ ጭምር ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ።
የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና የፓርቲው ዋና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ፣ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሃይን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በውይይታቸውም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት እንዲሁም በብልጽግና ፓርቲ እና በቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ መካከል ያለውን ትብብርና ስትራቴጂያዊ አጋርነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።
አቶ አደም ፋራህ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት በኢትዮጵያና በቻይና መካከል ያለው ዘመናትን ያስቆጠረ ወዳጅነት እና ሁሉን አቀፍ የሁልጊዜ ስትራቴጂካዊ አጋርነት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ እና በልማት ዘርፎች ያለውን ትብብር ለማስፋት የሚያስችል ነው።
ይህ ግንኙነትም በተለይም በልማት ዘርፎች ያለውን ትብብር ለማስፋት ጠንካራ መሠረት የሚጥል መሆኑን ገልጸዋል።
አምባሳደር ቼን ሃይ በበኩላቸው ብልጽግና ፓርቲ በኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ብልጽግናን፣ ሀገራዊ ልማትንና ተቋማዊ ሽግግርን እውን ለማድረግ እያከናወነ ላለው ጥረት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
በተለይም የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት መጠናቀቅን፣ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብርን፣ የሀገራዊ ምክክር ሂደትን፣ ለ32ኛው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) እየተደረገ ያለውን ዝግጅት እንዲሁም ሁለተኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ (APPS 2026) በአዲስ አበባ በስኬት መካሄዱን በልዩ ሁኔታ አንስተዋል።
አምባሳደሩ እነዚህ ጉዳዮች ለኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ልማትና ስትራቴጂካዊ አጀንዳ ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው መግለጻቸውን ከብልጽግና ፓርቲ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።