በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከ8 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ይለማል - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከ8 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ይለማል
ዲምቱ፣ ህዳር 3/2019(ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከ8 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ወደ ስራ መገባቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በወላይታ ዞን የ2019 ዓ.ም የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር "የውሃ ጸጋችንን አሟጠን በመጠቀም ከዝናብ ጥገኝነት የተላቀቀ ግብርናን እውን ለማድረግ እንሠራለን!" በሚል መሪ ሐሳብ በዱጉና ፋንጎ ወረዳ ብላቴ ኤታ ቀበሌ ተካሄዷል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ካርታ ካስኬ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ግብርናን ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሠራ ይገኛል።
ለበጋ መስኖ ልማቱ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ልዩ ትኩረት መሰጠቱንም ጠቁመዋል።
በዚህም በዘንድሮ የመስኖ ልማት ከ8 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ እንደሚለማ ገልጸዋል።
በበጋ ወራት የመስኖ ልማትን በማሳካት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተሠራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ ናቸው።
ከዚህ መነሻ በዘንድሮ መስኖ ልማት በመጀመሪያውና በሁለተኛው ዙር 2 ሺህ 100 ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ እንደሚሸፈን አስታውቀዋል።
የዱጉና ፋንጎ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘካሪያስ ዎንታሞ በበኩላቸው፣ ከመደመር መንግሥት ዋነኛ ኢኒሼቲቮች አንዱ በሆነው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ስንዴን በማምረት የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
በበጋ መስኖ ስንዴ 472 ሄክታር ማሳ በማልማት 16 ሺህ 48 ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።
የቀበሌው አርሶ አደሮች ኢዮብ ግያና አክሊሉ ገበየሁ እንዳሉት፣ ከዚህ ቀደም በዝናብ ጥገኛ ሆነው በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ በማምረት እምብዛም ሳይጠቀሙ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ሕይወት ሲመሩ ቆይተዋል።
አሁን ግን የመስኖ ሥራ ከጀመሩ ወዲህ በዓመት እስከ ሦስት ጊዜ በኩታ ገጠም በማምረት በየግላቸው እስከ 50 ኩንታል ምርት ማግኘት መጀመራቸውን ገልጸው፣ ዘንድሮም ማሳቸውን እያዘጋጁ መሆኑን ተናግረዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የክልል፣ የዞንና የወረዳ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎችና የአካባቢው አርሶ አደሮች ተገኝተዋል።