ቀጥታ፡

የሐረርጌ ጤና ምርምር ማዕከል በእናቶችና ጨቅላ ሕጻናት ጤና ላይ ተጨባጭ የምርምር ውጤቶችን እያፈለቀ ነው - የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ

አዲስ አበባ፤ህዳር 3/2019(ኢዜአ)፦የሐረርጌ ጤና ምርምር ማዕከል በእናቶችና ጨቅላ ሕጻናት ጤና ላይ ተጨባጭ የምርምር ውጤቶችን እያፈለቀ መሆኑን ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ገለጸ።

ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ

በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የሐረርጌ የጤና ምርምር ማዕከል የተመሰረተበትን 10ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በእናቶች ጤናና ጨቅላ ሕጻናት ሞት መንስኤ ላይ ዓለም አቀፍ የምርምር ሲምፖዚየም እያካሄደ ይገኛል።


 

የዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር መንግስቱ ዑርጌ በዚሁ ወቅት፤ የዩኒቨርሲቲው ‘የሐረርጌ ሔልዝ ሪሰርች’ ፕሮጀክት ከ10 ዓመት በፊት ወደ ሥራ መግባቱን አስታውሰዋል።

በአዲስ አበባ መካሄድ የጀመረው የዩኒቨርሲቲው ዓለም አቀፍ የምርምር ሲምፖዚየም የአስር ዓመታት የጥናትና ምርምር ውጤቶችን በመገምገም ለቀጣዮቹ አስር ዓመታት ዕቅድ ለማዘጋጀት ያለመ ነው ብለዋል።

‘የሐረርጌ ሔልዝ ሪሰርች’ ፕሮጀክትም ከአስር ዓመታት በፊት በጤና ሚኒስቴርና አጋር አካላት ትብብር የእናቶችና ሕጻናት ሞት መንስኤ ላይ መረጃ መሰብሰብ የሚያስችል ጥናት መደረጉን ገልጸዋል።

በፕሮጀክቱ የጥናት ውጤትም በእርግዝና ወቅት የፎሊክ አሲድ በበቂ መጠን አለመውሰድና በንጥረ ነገር የበለፀገ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በእናቶችና ሕጻናት ጤና ላይ እክል እንደሚያሳድር አመላክተዋል።

በጥናት ውጤቱ መሰረት የእርግዝና ወቅት የጤና አጠባበቅና ክብካቤ የሚያሻሽል ግንዛቤ በማሳደግ ለእናቶች ተገቢ የምክርና የሕክምና አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህም ጥናቱ በዳሰሰባቸው አካባቢዎች የጨቅላ ሕጻናትና የእናቶች ጤና አጠባበቅን በማሻሻል የሞት መጠን ምጣኔ ላይ ከፍተኛ ቅናሽ በማሳየት ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱን አስረድተዋል።

በቀጣይም ከሌሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር የፕሮጀክቱን የጥናት አድማስ በማስፋት በእናቶችና ሕጻናት ጤና ላይ የተሻለ ለውጥ ለማምጣት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።


 

በሐረርጌ የጤና ምርምር ማዕከል መሪ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ነጋ አሰፋ በበኩላቸው፤ ከለንደን ስኩል ኦፍ ሃይጅን ኤንድ ትሮፒካል ሜድስን ጋር በመተባበር የሕጻናት ጤና ክትትል ጥናት ማድረጉን ገልጸዋል።

በአስር ዓመታት ውስጥ በምሥራቅ ኢትዮጵያ ሲካሄድ የቆየውን ጥናትም በመቀሌ በማስጀመር በቀጣይም በዓርባ ምንጭ ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የእናቶችና ጨቅላ ሕጻናት የጤና እና ሕክምና አገልግሎት የፕሮጀክት ጥናት ውጤቶችን ለሚመለከታቸው አካላት በመስጠት ምክረ ሃሳብ እየቀረበ መሆኑን አስረድተዋል።

የፎሊክ አሲድ እጥረት፣ የሀብለሰረሰር ዘንግ ክፍተትና በእርግዝና ወቅት እናቶች ላይ የሚከሰት የደም ግፊት መንስኤዎችም በጥናት መለየታቸውን ተናግረዋል።

እ.ኤ.አ በ2015 በኢትዮጵያ የጨቅላ ሕጻናት ሞት 68 በመቶ አካባቢ እንደነበር በማስታወስ፤ አሁን ላይ የሞት ምጣኔው ወደ 44 በመቶ መቀነሱን ጥናቱ ማመላከቱን ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም