የመደመር መንግሥት የፀጥታ ኃይሉን የመፈጸም አቅም ከማሳደግ ባሻገር ከእድገቱም በቀጥታ ተጠቃሚ እንዲሆን እያደረገ ነው -ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር መንግሥት የፀጥታ ኃይሉን የመፈጸም አቅም ከማሳደግ ባሻገር ከእድገቱም በቀጥታ ተጠቃሚ እንዲሆን እያደረገ ነው -ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል
አዲስ አበባ፤ህዳር 3/2019(ኢዜአ)፦የመደመር መንግሥት የፀጥታ ኃይሉን የመፈጸም አቅም ከማሳደግ ባሻገር ከእድገቱም በቀጥታ ተጠቃሚ እንዲሆን እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።
ዛሬ በበኬ ከተማ አስተዳደር ከ1 ሺህ 600 በላይ ለሚሆኑ ለኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ አመራሮችና አባላት የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ርክክብ ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ መንግሥት በአእምሮና በአካል የዳበረ፣ ተልዕኮውን በብቃት የሚወጣ ሠራዊት ገንብቷል።
የሠራዊቱን የማድረግ አቅም ከመገንባት ጎን ለጎን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
ዛሬ በበኬ ከተማ አስተዳደር የተደረገው የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ርክክብ የሠራዊቱን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት በማሟላት ረገድ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልጸው፣ እርምጃው ከሀገር ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት ጋር በቀጥታ እንደሚተሳሰርም አስገንዝበዋል።
ሉዓላዊነት ማለት ድንበርን ከመጠበቅ ባሻገር የዜጎችን ክብር መጠበቅ ጭምር መሆኑን ገልጸው፤ ለፀጥታ አካላት የተደረገው የቤት መሥሪያ ቦታ ድጋፍም የዚሁ የሉዓላዊነት መገለጫ አንዱ አካል መሆኑን አብራርተዋል።
ይህ ተግባር ሁለንተናዊ ሉዓላዊነቷ የተረጋገጠ፣የዜጎች ክብር የተጠበቀባት፣ የፀናችና አምራች ኢትዮጵያን ለመገንባት ለተያዘው ራዕይ አንድ ወሳኝ ግብዓት መሆኑን ገልጸዋል።
ፌዴራል ፖሊስ የቤቶቹ ግንባታ በፍጥነት ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ታምራት ሙሉጌታ (ዶ/ር)፤ ይህ ክስተት ለዩኒቨርሲቲያችን ትልቅ ምዕራፍ ነው ብለዋል።
ይህ የክልሉ መንግሥት መልካም ፈቃድና የአመራሩ ያላሰለሰ ጥረት ውጤት መሆኑንም ገልጸው በዚህ የፖሊስ መንደር ከ1 ሺህ 600 በላይ የፌዴራል ፖሊስ አመራሮችና አባላት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።
ሠራዊቱን በሌሎችም የልማት ትሩፋቶች ተጠቃሚ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
የሰንዳፋ በኬ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቢ ተፈራ በበኩላቸው፤ የሰላም መሠረት ለሆነው የፖሊስ ሠራዊት መሬት ማቅረብ በመቻላችን ደስታ ይሰማናል ብለዋል።
በቀጣይም ከተማ አስተዳደሩ ከሠራዊቱ ጎን በመቆም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።የቤት መሥሪያ ቦታ የተሰጣቸው የፌዴራል ፖሊስ አባላትም የሀገራችንን ሉዓላዊነት፣ የሕዝባችንን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር እየተጋን እንገኛለን ብለዋል።
መንግሥት ለዚህ ውለታቸው እውቅናና ክብር በመስጠት ይህንን የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ በማቅረቡ ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል።