በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቡናን ለመጀመሪያ ጊዜ በኩታ ገጠም በመስኖ የማልማት ሥራ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቡናን ለመጀመሪያ ጊዜ በኩታ ገጠም በመስኖ የማልማት ሥራ ተጀመረ
ወላይታ ሶዶ፣ ሕዳር 3/2019 (ኢዜአ):-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የቡና ልማትና ምርታማነትን ለማሳደግ ቡናን ለመጀመሪያ ጊዜ በኩታ ገጠም በመስኖ የማልማት ሥራ መጀመሩን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በወላይታ ዞን ድጉና ፋንጎ ወረዳ ከ4 ነጥብ 5 ሄክታር በላይ በሚሆን ማሳ ላይ ቡናን ለመጀመሪያ ጊዜ በኩታ ገጠም በመስኖ የማልማት ሥራ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።
የኩታ ገጠም ልማት መርሐ-ግብሩን ያስጀመሩት የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ካርታ ካስኬ የቡና ልማትን በኩታ ገጠም ማካሄድ ምርታማነትን ለማሳደግና የምርት ጥራትን ለማሻሻል ወሳኝ ሚና አለው።
ልማቱም የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን፣ ተገቢ የእርሻ ቴክኖሎጂዎችንና ዘመናዊ የአመራረት ሥርዓቶችን በመጠቀም የሚካሄድ መሆኑን ገልጸዋል።
በመስኖ የሚካሄደው የክላስተር ልማት የቡና ምርትን በመጠንም ሆነ በጥራት በማሳደግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ሰፊ ዕድል እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።
በክልሉ ውሀ ገብ በሆኑና ለቡና ልማት ምቹ በሆኑ አካባቢዎች በመስኖ ታግዞ ቡናን የማልማት ሥራ ለመጀመሪያ ጊዜ መጀመሩን የገለጹት ቢሮ ሀላፊው፣ በክልሉ የቡና ልማት እንደ አንድ ኢኒሼቲቭ ተይዞ ወደ ሥራ ተገብቷል ብለዋል።
በቀጣይ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር አካል ተደርጎ እንደሚሰራ ጠቁመው ለዚህም፣ በየደረጃው ያለ አመራርና ባለሙያ ለአርሶ አደሩ ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።
በዛሬው እለትም ለቆላማ አካባቢዎች የሚሆን የቡና ዝርያ ተለይቶ ለመጀመሪያ ጊዜ በመስኖ መተከሉን ገልጸው፣ በቀጣይም በሁሉም ወረዳዎች ቡናን በመስኖ ማልማት በስፋት ይከናወናል ብለዋል።
የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ በበኩላቸው እንዳሉት፤ በዞኑ ቡናን በኩታ ገጠም ማልማት የመደመር መንግስት ዋነኛ ኢኒሼቲቭ ተደርጎ በንቅናቄ እየተመራ ይገኛል።
አርሶ አደሩ ከዘርፉ የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆን፣ ይህንን ምርጥ የቡና ዘር ለአካባቢው አርሶ አደሮች ተደራሽ ለማድረግ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የቡና ልማትን በኩታ ገጠም ማልማት የአርሶ አደሩን የኢኮኖሚ አቅም ለማጠናከርና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ አቅም ያለው ተግባር መሆኑንም ዋና አስተዳዳሪው አመልክተዋል።
በመሆኑም ይህንን ተግባር በሁሉም ወረዳዎች አጠናክሮ ለማስቀጠል ልማቱ በልዩ ትኩረት እንደሚመራም ገልጸዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የክልል፣ የዞንና የወረዳ ሥራ ኃላፊዎች፣ የግብርና ባለሙያዎችና ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።