ቀጥታ፡

ሕብረተሰቡ ለዓይን ብሌን ልገሳ በጎ ፈቃደኝነቱን ሊያሳይ ይገባል

አዲስ አበባ፤ህዳር 3/2019 (ኢዜአ)፦ ሀብረተሰቡ ለዓይን ብሌን ልገሳ በጎ ፈቃደኝነቱን ሊያሳይ እንደሚገባ ተገለጸ።

የዓይን ብሌን ልገሳ በሁሉም ሃይማኖቶች አስተምህሮ የተደገፈ እና ዕድሜ የማይለይ መሆኑም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ከኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በመተባበር ዓለም አቀፍ የዓይን ብሌን ልገሳ ወርን አስመልክቶ የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጤናዬ ደምሴ እንደተናገሩት፣ በኢትዮጵያ በዓይን ብሌን ጉዳት ሳቢያ ብርሃናቸውን ያጡ በርካታ ወገኖች ያሉ ሲሆን፣ ለዚህም ብቸኛው መፍትሔ ከሰው ልጆች የሚገኝ የዓይን ብሌን ልገሳ ብቻ ነው።

የዓይን ብሌን ልገሳ የሚፈጸመው አንድ ሰው ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየ በኋላ ብቻ መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ፣ ሂደቱም የሟችን አስክሬን ክብርና ገጽታ በማይነካ መልኩ በሰለጠኑ ባለሙያዎች እንደሚከናወን አስታውቀዋል።

አገልግሎቱ የዓይን ብሌን ለሚፈልጉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸው፣ የተጀመሩ ሥራዎችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

በዚህም መሠረት በጎ ፈቃደኞች ከሕልፈታቸው በኋላ የዓይን ብሌናቸውን በመለገስ ሌሎች ወገኖች የሕይወት ብርሃን እንዲያዩ ለማስቻል ሰፊ የንቅናቄ ሥራዎች እንደሚከናወኑ አመላክተዋል።

የግንዛቤ ማስጨበጫ ወሩ ኅብረተሰቡ ከሕይወት ሕልፈት በኋላ የዓይን ብሌኑን በመለገስ ለተቸገሩ ወገኖች ብርሃን እንዲሰጥ ግንዛቤና ንቅናቄ ለመፍጠር ያለመ መሆኑንም ተናግረዋል።

የሃይማኖት አባቶችም ኅብረተሰቡን በማንቃትና ይህንን በጎ ተግባር ወደ መሬት በማውረድ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በበጀት ዓመቱ 5 ሺህ ሰዎች የዓይን ብሌን ለመለገስ ቃል እንዲገቡ ለማድረግ የታቀደ ሲሆን፣ በኅዳር ወር ብቻ 300 ሰዎች ቃል እንዲገቡ እንደሚደረግ ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምክትል ጠቅላይ ጸሐፊ ሐጂ መስዑድ አደም በበኩላቸው፣ የዓይን ብሌን ልገሳ ከየትኛውም ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ጋር የማይጋጭና ሰውን የመርዳት እና የበጎ አድራጎት ትዕዛዝን የሚፈጽም ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

ሁሉም ሃይማኖቶች ሰውን መውደድ፣ መርዳት እና ሕይወትን ማዳን የሚያስተምሩ በመሆናቸው፣ ሰዎች ከሞቱ በኋላ የዓይን ብሌናቸውን ለተቸገሩ ወገኖች በበጎነት መለገስ የላቀ የሰብአዊነት እና የመንፈሳዊነት ልዕልና ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

በሕይወት እያለን ብቻ ሳይሆን ካለፍንም በኋላ ለወገኖቻችን የመድረስ ባህልን ማዳበር የፈጣሪን ፈቃድ መፈጸም መሆኑን በመግለጽ፣ ምዕመናን የልገሳ ቃል እንዲገቡ ጥሪ አቅርበዋል።

የሟች ቤተሰቦች የሟቹን የልገሳ ቃል በማክበርና በመተባበር መንፈሳዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም