በሕብረ ቀለማት ያሸበረቀው ፍል ውሃ- አለሎበድ - ኢዜአ አማርኛ
በሕብረ ቀለማት ያሸበረቀው ፍል ውሃ- አለሎበድ
በሰለሞን ብርሀኑ (ሰመራ - ኢዜአ)
እየተዝናኑ ይታከሙበታል፤ እየታከሙም ይዝናኑበታል - የተፈጥሮ ችሮታ በተለገሰው የአለሎበድ ፍል ውሃ። ፍል ውሃው የአፋር ክልል መናገሻ ከሆነችው ሰመራ ከተማ በ20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው የሚገኘው። በአውሳ ረሱ ዞን ዱብቲ ወረዳ ደበሊና ሃሊባይሪ ቀበሌ ተንጣሎ የሚታየው ፍል ውሃ በሕብረ ቀለማት ያሸበረቀና የተዋበ የቱሪስት መዳረሻም ነው። ከመሬት ውስጥ እየተፍለቀለ የሚወጣው ውሃ ሥፍራውን ከሚያውደው እንፋሎቱ ጋር ተዳምሮ አካባቢውን ልዮ ውበት አጎናጽፎታል።
በአካባቢው አጠራር አለሎበድ የሚባለው ይሄ የፍል ውሃ ሥፍራ በቀለማት ያሸበረቀ ከመሆኑ የተነሳ የቱሪስትን ቀልብ ይይዛል። በዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚነገረው ከሆነ የውሃው ትኩሳት እስከ 97 ዲግሪ ሴልሽየስ እንደሚደርስ ይነገርለታል። የፍል ውሃ ምድሩ በጀብደኛ ቱሪስቶች እጅግ ተመራጭና የሚወደድ መሆኑን ያዩት ሁሉ ይመሰክራሉ።
አለሎበድን ከሌሎች የተፈጥሮ ውሃ ምንጮች የሚለየው ከምድር ውስጥ በሚመነጨው ሙቀት የሚሞቀው ውሃ በተለያዩ ጉድጓዶች ተከማችቶ መገኘቱ ነው። የአለሎበድ ፍል ውሃ ሙቀት በአማካይ እስከ 97 ዲግሪ ሴልሽየስ የሚደርስ ሲሆን የውሃ ጥርቅሞቹ በአረንጓዴ፣ ሰማያዊ፣ ቢጫና ቡናማ ቀለማት አሸብርቀውና ተሰናስለው ሲታዩ ሌላኛው ድምቀቱ ይሆናሉ።
አለሎበድን ከሚያስደንቁ የተፈጥሮ ክስተቶች መካከል ሌላኛው ደግሞ ከምድር ውስጥ የሚያወጣው እንፋሎት ነው። ከመሬት ሥር የሚወጣው ውሃ ሙቀት ከፍተኛ በመሆኑ በውሃው ላይ የሚፈጠረው እንፋሎት ወደ አየር ይወጣል። በተለይም አላሎበዳ ስፖውተር (Allalobeda Spouter) የተሰኘው ፍል ውሃ ከስድስት እስከ 30 ሜትር የሚደርስ ከፍታ ላይ ሲወነጨፍ ይታያል።ክስተቱ በምድር ውስጥ ያለው ሙቀት ውሃን በማሞቅ ግፊት እንዲፈጠር እና ውሃው በጠባብ መውጫ በኩል ወደ ላይ እንዲወጣ ከሚያደርገው የተፈጥሮ ሂደት ጋር እንደሚያያዝ የከርሰ ምድር ባለሞያዎች ያስረዳሉ።
አለሎበድ የሚገኝበት አካባቢ የቀይ ባሕርና የኤዴን ባሕረ ሰላጤ የስብራት መስመሮች ከታላቁ የስምጥ ሸለቆ ጋር በሚገናኙበት ልዩ የምድር አቀማመጥ ውስጥ የሚገኝ መሆኑም ይነገራል። በዚህ የምድር አቀማመጥ ምክንያት የምድር ንጣፍ በተለያዩ ስብራቶች የተከፋፈለ ሲሆን ከምድር ጥልቅ ክፍል የሚመነጨው ሙቀት ወደ ላይኛው ክፍል እንዲደርስ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮለታል።
በአለሎበድ የተካሄዱ የጂኦፊዚክስና የጂኦኬሚስትሪ ጥናቶችም ከምድር ውስጥ የሚመነጭ እንፋሎትን የያዘ የጂኦተርማል ሥርዓት መኖሩን ያመለክታሉ። ይህም አካባቢው ከቱሪዝም ባሻገር ለጂኦተርማል ኃይል ምርምርና ልማት ያለውን አቅም ያሳያል።
የአለሎበድ ፍል ውሃ በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ለምግብ ማብሰያነትና ለመታጠቢያነት ጭምር የሚገለገሉበት ሲሆን በርካታ የውጭና የሀገር ውስጥ ቱሪስቶችም ወደአካባቢው እየመጡ ይጎበኙታል። ከዳሎል ባለቀለም የተፈጥሮ ገጽታ፣ ከኤርታሌ እሳተ ገሞራና ከአፋምቦ ሐይቅ በተጨማሪ አለሎበድ የአፋር ክልሉ የቱሪዝም መስህብ ሆኖ የሚያገለግል ትልቅ ሃብት ነው። የቱሪዝም ሀብቱን በሚገባ ለመጠቀም ግን የመንገድ መሠረተ ልማትን ማሻሻል ያስፈልጋል። ዘመናዊ የጎብኚዎች ማረፊያና የመረጃ ማዕከላትን ማዘጋጀትም እንዲሁ ወሳኝ መሆኑ ይታመናል።
ሲያዩት የተመልካችን ቀልብ በመሳብ አንዳች የሀሴት ስሜት የሚፈጥረው ይህ ስፍራ ከልማት ርቆ ቆይቷል። የክልሉ ጸጋ የሆነውን ይህን የተፈጥሮ ሀብት አልምቶ መጠቀም ከተቻለ አንድ የቱሪስት መዳረሻ ሆኖ የማገልገል አቅም ከፍተኛ ነው።
ውበቱ ሊገልጥና ፈዋሹነቱንም በይፋ ሊያውጅ እየተንደረደረ ያለውን አለሎበድ በማልማት ጠቀሜታውን ለማጉላት ትኩረት መሰጠቱ ተገልጿል። የገበታ ለሀገር ኘሮጀክት አካል የሆነውና በአፋር ክልል አዋሽ ብሔራዊ ፓርክ አቅራቢያ የሚገኘው "ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ" ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ሲመረቅ ይሄም ስፍራ በቀጣይ እንደሚለማ ተመላክቷል። የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ በክልሉ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለይቶ ከማልማት አኳያ አለሎበድ ፍል ውሃን ለቀጣይ በዕቅድ መያዙን በዚህ ወቅት ይፋ አደርገዋል።
እናም በቀጣይ አለሎበድ ፍል ውሃ ሲገነባ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ከተገነባው የኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ እና ሌሎችም የቱሪስት መስህቦች ጋር ተዳምረው የአፋርን የቱሪስት መዳረሻነት ከፍ ያደርጋሉ። ይህም የአካባቢው ነዋሪዎች በዘርፉ ተጠቃሚ ከማደረግ ባለፈ የክልሉን ገቢ በማሳደግ በኩልም ሚናው የላቀ እንደሚሆን ሳይታለም የተፈታ ነው።