ቀጥታ፡

በአሪ ዞን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር የተጀመሩ ሥራዎች ውጤት እያመጡ ነው

ጂንካ፤ ሕዳር 3/2019 (ኢዜአ)፡-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አሪ ዞን  ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር የተጀመሩ ሥራዎች ውጤት እያመጡ መሆናቸውን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

የአሪ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጉራልቅ ይዥማልቅ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ለመከላከል የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

በተለይ በዞኑ የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ ልማት ለአፈር ለምነት መጠበቅ እንዲሁም ለኑሮና ለእርሻ ተስማሚ ስነምህዳር በመፍጠር ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።

በዞኑ በቤተሰብ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትን ለመከላከልና ለአደጋ ሥጋት የማይበገር ማህበረሰብ ለመፍጠር  የሌማት ትሩፋት መርሀግብር በስፋት እየተተገበረና ለውጥም እየተገኘበት ይገኛል ብለዋል።

በዚህም የዶሮ፣ ዕንቁላል፣ የአሣ ፣ የማርና የወተት ምርት በእጥፍ እያደገ መምጣቱን ነው የገለጹት።

በዞኑ የአደጋ ሥጋትን ለመከላከልና ከተረጂነት ለመውጣት ትኩረት ከተደረገባቸው ሌላው ምርታማነትን በእጥፍ ማሳደግ መሆኑን ጠቁመው ለዚህም የኩታ ገጠም እርሻዎችን የማስፋፋት ሥራ በትኩረት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በልማቱም በየዓመቱ ከ7 ሚሊዮን ኩንታል በታች ይገኝ የነበረውን አጠቃላይ የሰብል ምርት ወደ 15 ሚሊዮን ኩንታል ማሳደግ እንደተቻለ አቶ ጉራልቅ አመልክተዋል።


 

እንደእሳቸው ገለጻ አርሶ አደሮች ባላቸው አነስተኛ ማሳ የስብጥር አመራረት ዘዴን በመከተል በትንሽ ቦታ ብዙ ጥቅሞችን የሚያገኙበት ስልት ተግባራዊ ተደርጓል።

የአሪ ዞን ለአፈር መንሸራተት አደጋ በብዛት ተጋላጭ እንደሆነ የገለጹት ሀላፊው፣ በነዚህ አካባቢዎች የተፋሰስ ልማት በማከናወን የተራቆቱ አካባቢዎችን በደን የመሸፈን እና ህብረተሰቡን ስለ አደጋ መከላከል የማስገንዘብ ሥራ በስፋት መሰራቱንም ጠቁመዋል።

ድንገተኛ አደጋ ቢከሰት አፋጣኝ ምላሽ መስጠት እንዲቻልም ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ ተጠባባቂ ገንዘብ ተቀማጭ የተደረገ ሲሆን፣ ከ464 ኩንታል በላይ እህልም በመጋዘን እንዲከማች መደረጉን ገልጸዋል።

 


በቀጣይም ለአደጋ ሥጋት የማይበገር ዘመናዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር በመዘርጋት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ማህበረሰብ ለመፍጠር ትኩረት መሰጠቱን አስታውቀዋል።

በአሪ ዞን አስተያየታቸውን ከሰጡ አርሶ አደሮች መካከል ባካዳውላ አሪ ወረዳ የሚኖሩት አርሶ አደር ሀዝሚ ማርቆስ እና አርሶ አደር አለሙ አንክሺ እንዳሉት፣ የአየር ንብረት ለውጥ በሚያሳድረው ተፅዕኖና መፍትሄው ላይ ከግብርና ባለሙያዎች ትምህርት አግኝተዋል።

በዚህም በዝናብ ወቅቶች ከሚያከናውኑት የግብርና ልማት ሥራ በተጨማሪ የመስኖ ውሃ በመጠቀም፣ በማሳቸው ውሃ በማሰባሰብ እና የመሬት እርጥበትን በመጠቀም የእርሻ ሥራቸውን እያከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የወተት ላም፣ ዶሮ፣ አሣ እና ንብ በማርባት ተጨማሪ ገቢ የሚያገኙበትን ዕውቀት ከግብርና ባለሙያዎች እንዳገኙ ጠቁመው፤ ይህንንም ወደተግባር በመቀየራቸው ገቢያቸውን እያሳደጉ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም