ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የደንና የአየር ንብረት ተግባርን ለማሳደግ ቁርጠኛ ናት

አዲስ አበባ፤ ህዳር 3/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የደንና የአየር ንብረት ተግባርን ለማሳደግ ቁርጠኛ እና ዝግጁ መሆኗን የብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስትር በረከት ፍስሃፅዮን ገለጹ።

31ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ “ጉዞ ወደ ዘላቂ፣ አይበገሬነት እና ፍትሃዊነት ወደተረጋገጠበት መጻኢ ዘመን” በሚል መሪ ቃል በቱርኪዬ አንታሊያ እየተካሄደ ይገኛል።

ኢትዮጵያ በኮፕ 31 የመሪዎች ዝግጅት ላይ “ደኖችና የአየር ንብረት ጥበቃ ተግባር፡ ደኖች የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም ያላቸው አስተዋጽኦ” በሚል ርዕስ በተካሄደው መድረክ በመሳተፍ፣ ዓለም አቀፍ የደንና የአየር ንብረት ተግባርን ለማሳደግ ያላትን ጽኑ ቁርጠኝነት አረጋግጣለች።

በመድረኩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስትር አቶ በረከት ፍስሃፅዮን፣ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ በተደረገውና ከ56 ቢሊዮን በላይ ችግኞች በተተከሉበት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የተመዘገበውን ተጨባጭ ለውጥ አንስተዋል።

አክለውም ደኖች ለአየር ንብረት ጽናት፣ ለብዝኃ ሕይወት ጥበቃ፣ ለዘላቂ የኑሮ ምንጮች እንዲሁም አረንጓዴ የሥራ እድሎችን ለመፍጠር ያላቸውን ወሳኝ ሚና አጉልተው ገልጸዋል።

ቀጣዩን የኮፕ 32 ጉባኤ የምታስተናግድ ሀገር እንደመሆኗ መጠን፣ ኢትዮጵያ የተራቆቱ የደን መሬቶችን መልሶ የማልማት ሥራን ይበልጥ ለማፋጠን እና እ.ኤ.አ በ2030 የደን ጭፍጨፋን ለማስቆምና የደን መመናመንን ለመቀልበስ የተቀመጠውን ዓለም አቀፍ ግብ ለማሳካት፣ የተጠናከረ ዓለም አቀፍ አጋርነት፣ ኢንቨስትመንት እና የጋራ ተግባር እንዲኖር ጥሪዋን አቅርባለች።

#COP31 #COP32 #GreenLegacy #ClimateAction

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም