ኢትዮጵያ እና ዩናይትድ ኪንግደም በኮፕ 32 ዝግጅትና በአየር ንብረት ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመስራት ተስማሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ዩናይትድ ኪንግደም በኮፕ 32 ዝግጅትና በአየር ንብረት ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመስራት ተስማሙ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 3/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ዩናይትድ ኪንግደም በኮፕ 32 ዝግጅትና በአየር ንብረት ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ እንደሚሰሩ አስታወቁ።
31ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በቱርኪዬ አንታሊያ እየተካሄደ ይገኛል።
“ጉዞ ወደ ዘላቂ፣ አይበገሬነት እና ፍትሃዊነት ወደተረጋገጠበት መጻኢ ዘመን” የጉባኤው መሪ ቃል ነው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የኮፕ 32 ተመራጭ ፕሬዚዳንት ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) እንዲሁም የገንዘብ ሚኒስትርና የኮፕ 32 ዋና ተደራዳሪ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ከጉባኤው ጎን ለጎን ከዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሴክሬታሪ ኤድ ሚሊባንድ ጋር ተወያይተዋል።
በዚሁ ወቅት ተመራጩ ፕሬዚዳንት ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ዘርፍ እያከናወነቻቸው ያሉ ተግባራዊ ውጥኖችን ያብራሩ ሲሆን፤ ለአየር ንብረት ለውጥ መንስኤ የሚሆኑ ልቀቶችን መቀነስ ያለው አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤድ ሚሊባንድ በበኩላቸው የበካይ ጋዝ ልቀትን መቀነስ የአየር ንብረት ተግዳሮቶችን ለመፍታት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ዩናይትድ ኪንግደም በዚህ ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት ለመስራት ፍላጎት እንዳላት የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ለኮፕ 32 ዝግጅቶች እና ለኢትዮጵያ ቅድሚያ ጉዳዮች ድጋፍ ለማድረግ ሀገራቸው ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።