በክልሉ አቮካዶን በክላስተር በማልማት የአርሶ አደሩን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ አቮካዶን በክላስተር በማልማት የአርሶ አደሩን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት ተደርጓል
ባህር ዳር፣ ህዳር3/2018 (ኢዜአ) ፡-በአማራ ክልል አቮካዶን በክላስተር በማልማት የአርሶ አደሩን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በቢሮው የብሔራዊ አቮካዶ ልማት ፕሮግራም አስተባባሪ ይበልጣል ወንድምነው ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በክልሉ የአቮካዶ ልማትን በማስፋፋት የአርሶ አደሩ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያደገ መጥቷል።
በዚህም ባለፉት ዓመታት ከ15 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በአቮካዶ የለማ ሲሆን፣ ምርቱን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ በማቅረብ አርሶ አደሩን የላቀ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት በ39 ወረዳዎች 32 ሺህ 433 ሄክታር መሬት በክላስተር ለማልማት ግብ ተይዞ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በአቮካዶ ልማቱም 129 ሺህ አርሶ አደሮች የሚሳተፉ ሲሆን፣ ምርቱን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የማቅረብ ሥራ እንደሚከናወን ገልጸዋል።
ለዚህም ባለፈው የክረምት ወቅት ብቻ በ700 ሄክታር መሬት ላይ የተሻሻሉ የአቮካዶ ችግኞችን በክላስተር በመትከል እንክብካቤ እየተደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
በተለይ በያዝነው ዓመት የበጋ ወቅት በመስኖና በመጪው ክረምት 14 ሺህ ሄክታር መሬት በአቮካዶ ችግኝ ለመሸፈን ከወዲሁ ችግኝ የማዘጋጀት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።
የአቮካዶ ልማት መስፋፋት የሥርዓተ ምግብን ከማሻሻልና የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ፣ ለመዋቢያ ቅባት አምራች ኢንዱስትሪዎች በግብዓትነት እንደሚውልም አስታውቀዋል።
በሰሜን ጎጃም ዞን የሰሜን ሜጫ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር መጣዓለም ፈንታሁን እንዳሉት፣ ቀደም ሲል በሁለት ሄክታር መሬት ላይ አቮካዶ ተክለው በማልማት ላይ ይገኛሉ።
በየዓመቱ የሚሰበስቡትን ምርት ወደ ገበያ በማቅረብ የተሻለ ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ ጠቅሰው፣ በቀጣይም ልማቱን ለማስፋፋት እየሠሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ዘንድሮ ሩብ ሄክታር የሚጠጋ መሬትን የአቮካዶ ችግኝ ተክለው በመስኖ ለማልማት እየተዘጋጁ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዚሁ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ገብሬ አሞኘ ናቸው።
ቀደም ሲል ተክለው እያለሙት ካለው ግማሽ ሄክታር መሬት ከ30 ኩንታል የሚበልጥ ምርት ሰብስበው ለገበያ በማቅረብ የተሻለ ተጠቃሚ እንደሆኑም አስረድተዋል።