ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ሕጋዊ መሰረት ያለው ብሔራዊ ፍላጎት ነው- የቀድሞው የኮትዲቯር ጠቅላይ ሚኒስትር ፓስካል አፊ ንጌሳን

አዲስ አበባ፤ ህዳር 3/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገው ጥረት ህጋዊ መሰረት ያለው ብሔራዊ ፍላጎት መሆኑን የቀድሞው የኮትዲቯር ጠቅላይ ሚኒስትር እና የሀገሪቱ የሕዝባዊ ግንባር (FPI) ፕሬዝዳንት ፓስካል አፊ ንጌሳን ገለጹ።

ኢትዮጵያ ያለችበትን ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ፣ታሪካዊ ቁርኝት እና እያደገ የመጣውን የኢኮኖሚ ፍላጎት መሠረት በማድረግ ወደ ቀይ ባሕር ዘላቂና አስተማማኝ መውጫ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በር ተዘግቶባትና የጂኦግራፊ እስረኛ ሆና መቀጠል እንደማትችል መናገራቸው ይታወሳል።

በዚህም ኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄዋ ምላሽ እንዲያገኝ ሠላማዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና በንግድ ሕግ ላይ የተመሰረተ አካሄዶችን እንደምትከተል በተደጋጋሚ አረጋግጣለች።

የቀድሞው የኮትዲቯር ጠቅላይ ሚኒስትር ፓስካል አፊ ንጌሳን የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ተገቢውን ዕውቅና ማግኘት እንዳለበት ለኢዜአ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፍላጎት ቀጣናውን የጋራ ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ በውይይት እና በስምምነት ምላሽ ማግኘት እንደሚገባም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ከሰፊው ጂኦፖለቲካዊ ሁኔታና ከአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የጋራ መፃኢ ዕድል አንጻር መቃኘት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ፍላጎት በሁሉም ወገኖች ዘንድ ተቀባይነት ባለው መንገድ እንደሚፈታ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በመሆኑም በጉዳዩ ላይ የሰከነ እና ገንቢ ውይይት ማድረግ እንደሚገባም ጠቅሰው፤ አፍሪካዊ መፍትሔዎች ለዘላቂ ሰላም እና ብልጽግና ወሳኝ ናቸው ብለዋል።

አፍሪካ ማደግ የምትችለው በአንድነት ነው፤ እውነተኛ አንድነት ደግሞ በሀሳብና በሀብት መጋራት ሊገለጽ ይገባል ብለዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያን የባህር በር የማግኘት ፍላጎት ከዚህ ማዕቀፍ አንጻር ማየት እንደሚገባም ነው የቀድሞው የኮትዲቯር ጠቅላይ ሚኒስትር እና የሀገሪቱ የሕዝባዊ ግንባር (FPI) ፕሬዝዳንት ፓስካል አፊ ንጌሳን የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም