የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ለዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ጥበቃ ጥረት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው - ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ለዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ጥበቃ ጥረት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው - ምሁራን
ጅማ፤ህዳር 3/2019 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ እያከናወነች ያለው ተግባር የተፈጥሮ ሀብትን ከመጠበቅ ባለፈ፣ ለዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ጥረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የጅማ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናገሩ።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ ለመቋቋም እና የተራቆቱ አካባቢዎችን መልሶ ለማልማት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ሀገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ነድፋ በመተግበር ላይ ትገኛለች።
መርሃ ግብሩ ከአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ባሻገር የደን ሽፋንን በማሳደግ፣ የአፈር መሸርሸርን በመግታት እና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ወሳኝ መሠረት እየጣለ ይገኛል።
በዚህም ባለፉት ዓመታት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች ተተክለው እንክብካቤ እየተደረገላቸው ሲሆን፣ ተግባሩ በዓለም አቀፍ ደረጃም በአርዓያነት እየተጠቀሰ ይገኛል።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የግብርናና እንስሳት ሕክምና ኮሌጅ የሥነ ምህዳር መምህርና ተመራማሪ ጥበቡ አለሙ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ባለፉት ዓመታት በዘርፉ የተከናወነው ሥራ የመሬት መሸርሸርን ከመቀነስ ባለፈ የተበላሹና የደረቁ አካባቢዎችን መልሶ በማልማትና የደን ሽፋንን በማስፋት ረገድ ሰፊ ሚና እየተወጣ ይገኛል።
ሥራው የዝናብ ውሃን ለመያዝ፣ የአፈር እርጥበትን ለማስቀጠልና የጎርፍ አደጋን ለመቀነስ እንደሚያግዝ የገለጹት አለሙ (ዶ/ር)፤ መርሃ ግብሩ የሕዝብ ተሳትፎንና ማኅበራዊ ትስስርን በማጠናከር ለቀጣይ ትውልድ ጤናማ አካባቢ ለማስረከብም ያግዛል ብለዋል።
በተጨማሪም ለከተሞች ውበት፣ ለምግብ ዋስትናና ለሥራ ዕድል ፈጠራ የሚኖረው አስተዋጽኦ ጉልህ መሆኑን ጠቁመው፣ ኢትዮጵያ በዘርፉ እያከናወነች ያለው ተግባር ለሌሎች ሀገራትም ተሞክሮ የሚሆን መሆኑን አስረድተዋል።
በኮሌጁ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ጌትነት ሰይድ በበኩላቸው፤ መርሃ ግብሩ የአየር ንብረት ለውጥንና የአፈር መሸርሸርን በመከላከል የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ እያገዘ መሆኑን ገልጸዋል።
የአረንጓዴ አሻራ ሥራ ከበጋው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ተግባራት ጋር በተቀናጀ መልኩ መከናወኑ የከርሰ ምድርና የገጸ ምድር ውሃ ሀብትን ለማሳደግ እንደሚያግዝ ጠቅሰው፤ ይህም ለመስኖ ልማት መስፋፋትና ለግብርና ምርታማነት መጨመር ተጨማሪ አቅም እየፈጠረ መሆኑን አብራርተዋል።
ይህ የተቀናጀ ሥራ የአረንጓዴ ኢኮኖሚን ከማስፋት ባለፈ ለሀገራዊ፣ ለቀጣናዊና ለዓለም አቀፋዊ የአካባቢ ጥበቃ ጥረቶች የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ የCOP32 ጉባዔን ለማስተናገድ መመረጧም በአካባቢ ጥበቃና በአረንጓዴ ልማት ዘርፍ ያላትን ተሳትፎ በዓለም አቀፍ መድረክ ለማጠናከር ተጨማሪ ዕድል እንደሚፈጥር ምሁራኑ ጠቁመዋል።