ቀጥታ፡

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ሀገራዊ መግባባትን ለማጠናከር ጉልህ ሚና አለው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 3/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ሀገራዊ መግባባትን በማጠናከር የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ጉልህ ሚና እንዳለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።

21ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን "በብዝኃነት የደመቀች በምክክር የፀናች ሥልጡን ኢትዮጵያ" በሚል መሪ ሀሳብ ሕዳር 29 ቀን 2019 ዓም በኦሮሚያ ክልል ጅማ ከተማ ይከበራል።


 

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የዘንድሮው መሪ ሀሳብ የጋራ ቃል ኪዳን መሆኑን ታሳቢ በማድረግ የጋራ ዕቅድና የጋራ ግንዛቤ መፍጠር የሚያስችል የመሪ ሀሳብ ትንተና እና የኮሙኒኬሽን ስትራቴጂ የውይይት መድረክ አዘጋጅቷል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ደስታ ሌዳሞ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን አብሮነትን ያጎለብታል።

በተጨማሪም በኢትዮጵያ ገዥ ትርክት ግንባታ እንዲጠናከርና በትብብር የበለጸገች ሀገርን እውን ለማድረግ ያስችላል ብለዋል።


 

በኢትዮጵያ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ምልዓተ ህዝቡን በንቃት የሚያሳትፍ መሆኑን በማንሳት፤ መገናኛ ብዙሃን ለስኬታማነቱ መረጃ ተደራሽ በማድረግ በኩል ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ገለጸዋል።

በመሆኑም መገናኛ ብዙሃን ለበለፀገች ኢትዮጵያ እውን መሆን በመረጃ ላይ ተመስርተው ለህዝቡ ተደራሽ በመሆን ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ያዘጋጀው የመሪ ቃል ትንተናና የኮሙኒኬሽን ስትራቴጂ መድረክ የመገናኛ ብዙሃንና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ተዋንያን ተጨማሪ ግብዓት የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም