ኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከሞሮኮ ጋር ትጫወታለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከሞሮኮ ጋር ትጫወታለች
አዲስ አበባ፤ ህዳር 3/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ሁለተኛ ዙር ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታውን ዛሬ ከሞሮኮ ጋር ያደርጋል።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በድሬዳዋ ስታዲየም ይካሄዳል።
በአሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ የሚመራው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በመጀመሪያ ዙር ዩጋንዳ ራሷን በማግለሏ ምክንያት በፎርፌ ወደ ሁለተኛው ዙር አልፏል።
ብሔራዊ ቡድኑ ለሁለተኛ ዙር ጨዋታ ለሁለት ሳምንታት ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል።
አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ በቅድሚያ ለ31 ተጫዋቾች ጥሪ ካደረጉ በኋላ ተጨማሪ ሶስት ተጫዋቾችን ተጨምረው ወጣት ብሔራዊ ቡድኑ የቀጠለ ሲሆን ስብስቡን ወደ 23 ተጫዋች በመቀነስ ቡድኑ የመጨረሻ ዝግጅቱን በድሬዳዋ አከናውኗል።
በአሰልጣኝ ጃማል አይት ቤን ኢዲር የሚመራው የተጋጣሚው የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን 25 ወጣት ተጫዋቾችን ያካተተ ስብስብ በመያዝ ለጨዋታው ለአንድ ሳምንት ዝግጅት አድርጓል።
ሞሮኮ የወቅቱ ከ23 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ባለቤት ናት። በዚህም ለሁለተኛው ዙር ማጣሪያ በቀጥታ አልፋለች።
ሁለቱ ሀገራት በዚህ የዕድሜ እርከን እርስ በእርስ ሲገናኙ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
የብሔራዊ ቡድኖቹ የመልስ ጨዋታ ህዳር 8 2019 ዓ.ም በሞሮኮ ራባት ይካሄዳል።
በደርሶ መልስ የሚያሸንፈው ሀገር ወደ መጨረሻው ዙር ማጣሪያ ያልፋል።
ከ23 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ እ.አ.አ በ2027 በግብጽ አስተናጋጅነት ይካሄዳል።
በውድድሩ ላይ ግብጽን ጨምሮ ስምንት ሀገራት ይሳተፋሉ።
በአፍሪካ ዋንጫው ከአንድ እስከ ሶስት የሚወጡ ብሔራዊ ቡድኖች በቀጥታ እ.አ.አ በ2028 ሎስ አንጀለስ በሚካሄደው 34ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ይሳተፋሉ።
በውድድሩ አራተኛ ደረጃን ይዞ የሚያጠናቅቀው ቡድን ከሌላ አህጉር አራተኛ ደረጃን ከያዘ ቡድን ጋር ለሚደረግ የጥሎ ማለፍ (Play-off) ጨዋታ ያልፋል።