በተፈጥሮ ጋዝ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች የሀገር ሀብትን በውጤታማነት ለመጠቀም ያስችላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በተፈጥሮ ጋዝ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች የሀገር ሀብትን በውጤታማነት ለመጠቀም ያስችላሉ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 3/2019 (ኢዜአ)፦በተፈጥሮ ጋዝ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች የአየር ብክለትን በመቀነስ የሀገር ሀብትን በውጤታማነት ለመጠቀም እንደሚያግዙ የአዲስ አበባ ከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት ገለጸ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥቅምት 20 ቀን 2019 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ቀደም ሲል በነዳጅ ይሠሩ የነበሩ እና ወደ ተፈጥሮ ጋዝ የተቀየሩ የመጀመሪያዎቹ 26 የከተማ አውቶቡሶችን ሥራ ማስጀመራቸው ይታወቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ በቤንዚንና በናፍጣ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን ኢንጂን በመቀየር ወደ ተፈጥሮ ጋዝ የመቀየሩ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
ሀገር ውስጥ እያመረትን ያለነውን የተፈጥሮ ጋዝ በስፋት ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችሉ 400 አዳዲስ በተፈጥሮ ጋዝ የሚሠሩ አውቶቡሶች በቅርቡ ወደ ሀገር ውስጥ ይገባሉ ብለዋል።
በዚሁ ጉዳይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አካሉ አሰፋ፣ ይህ አሠራር የሀገር ሀብትን በውጤታማነት ለመጠቀም ትልቅ ታሪካዊ እርምጃ ነው፡፡
በተፈጥሮ ጋዝ የሚሠሩ አውቶቡሶች የትራንስፖርት እጥረትን ከማቃለልና ከአየር ንብረት ጥበቃ አኳያ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
የተፈጥሮ ጋዝ የካርቦን ልቀት እጅግ በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ ከተማዋን ከአየር ብክለት ለመጠበቅ በሚደረገው ጥረት ላይ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል።
በነዳጅ አቅርቦት መዘግየትና እጥረት ሳቢያ የሚፈጠሩ የትራንስፖርት አገልግሎቶች መቆራረጦችን ለመቅረፍ ይህ ትልቅ እርምጃ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የድርጅቱ የባስ ካፒቴኖች በበኩላቸው፤ አውቶቡሶቹ ከነዳጅ ወደ ተፈጥሮ ጋዝ መቀየራቸው እንደ ሀገር የአየር ብክለትን ከመከላከል አንጻር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።
ካነጋገርናቸው የባስ ካፒቴኖች መካከል ዳንኤል ደስታ፤ በተፈጥሮ ጋዝ የሚሠሩ አውቶቡሶች የሕዝብ ትራንስፖርት አሰጣጥ አገልግሎቱን ፈጣን፣ ንጹሕ እና አስተማማኝ በማድረግ በኩል ሚናው ትልቅ ነው ብለዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የባስ ካፒቴን ካሳሁን ብርሃኑ እንደገለጸው፤ ወደ ተፈጥሮ ጋዝ መቀየሩ የሀገር ውስጥ ሀብትን በውጤታማነት መጠቀም ያስችላል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ጭስ አልባ በመሆናቸው የአዲስ አበባን የአየር ብክለት ለመቀነስ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን በመግለጽ፤ ለናፍጣና ለቤንዚን የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ በማዳን በኩል ትልቅ ሚና እንዳለው አመልክተዋል።
ከትራንስፖርት ተጠቃሚዎች መካከል ወጣት ኬና ታደሰ እንዳለችው፤ በተፈጥሮ ጋዝ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ለአካባቢ ጥበቃ እና ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑን ገልጻለች።
ቀደም ሲል በነዳጅ ከሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ጋር ሲነጻጸር የእነዚህ ተሽከርካሪዎች የካርቦን ልቀት አነስተኛ መሆኑ ተጠቃሚዎች ጤና ላይ የሚደርሰውን ተጽዕኖ ለመቀነስ እገዛ እንዳለው ጠቁማለች።
ወጣት ቅዱስ ተገኑ በበኩሉ፤ በተፈጥሮ ጋዝ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎቹ ለተሳፋሪዎች ምቹና ከተማዋን የአየር ብክለት መቀነስ የሚያስችል መሆኑን አመልክቷል።