የአርባ ምንጭ ገጸ-በረከቶች - ኢዜአ አማርኛ
የአርባ ምንጭ ገጸ-በረከቶች
በሳሙኤል አየነው (ኢዜአ- አርባ ምንጭ)
የጥበብና የሙዚቃ ፈርጥ የነበረው አርቲስት አቡሌ ጨዶ፣ “ኑደሬይ ጋሞ ጎፋ ኦይቻ አርባ ምንጬ ሚዚሪ ካልሲ የደስ አባያ ጫሞ ሞሌ” በማለት በሙዚቃው ያወደሳቸው የአባያና ጫሞ ሀይቆች፣ የአርባምንጭ ከተማ የተፈጥሮ ውበትና የሀብት ምንጮች ናቸው። የዚህ ዘፈን መልእክትም "መኖሪያችን ጋሞ እና ጎፋ ነው፤ የአባያና ጫሞ ዓሣ መላውን አርባ ምንጭ አጥግቦ ይሸኛል" እንደማለት ነው። አዎ አባያና ጫሞ ከአርባ ምንጭም ባለፈ የሀገር የምግብ ዋስትና መሰረትና የቱሪዝም መስህብ በመሆን የሚያገለግሉ እምቅ ሃብቶች ናቸው።
የአርባ ምንጭ ከተማ በተፈጥሮ ውበቷ፣ በዓሣ ምርቷና በብዝሃ ሕይወቷ ከሚታወቁ የኢትዮጵያ ከተሞች መካከል ትጠቀሳለች። በተለይም የአባያና ጫሞ ሀይቆች እንዲሁም በመካከላቸው የሚገኘው የእግዜር ድልድይ ለከተማዋ የተለየ ገጽታ በመፍጠር ሁነኛ የቱሪዝም መስህብ ሆነው እያገለገሉ ነው።
ከአርባ ምንጭ ከተማ በስተምሥራቅ በ10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የአባያ ሀይቅ፣ 1 ሺህ 160 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ስፋትና 13 ሜትር የሚደርስ ጥልቀት አለው። የዐዞዎች፣ የጉማሬዎችና የተለያዩ የዓሣ ዝርያዎች መኖሪያ የሆነው የአባያ ሀይቅ 11 ደሴቶች ያሉት በመሆኑ ለጉብኝትና ለሽርሽር ተመራጭ ነው።
የጫሞ ሀይቅም ከአርባ ምንጭ ከተማ በስተደቡብ በ10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ የምሥራቅ አፍሪካ የስምጥ ሸለቆ ሀይቅ መሆኑ ይታወቃል። የ550 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋትና እስከ 13 ሜትር የሚደርስ ጥልቀት ያለው ሃይቅም ነው። የጫሞ ሀይቅ በዳርቻ የዓዞዎች መናገሻ ሲሆን የዐዞ ገበያ በመባል የሚታወቀው አካባቢም በቱሪስቶች ለጉብኝት የሚመረጥ አካባቢ ነው።
የአምስት ገባር ወንዞች ተቀባይ የሆነው የጫሞ ሀይቅ፣ በማራኪ የተፈጥሮ ገጽታው እና በብዝሃ ሕይወቱ የተለየ ስፍራ ያለው መሆኑም ይታወቃል። በርካታ ዐዞዎች፣ ጉማሬዎችና የተለያዩ የዓሣ ዝርያዎች የሚገኙትም በዚሁ ሐይቅ ሲሆን የጀልባ ሽርሽር የሚደረግበት ተመራጭና ተወዳጅ አካባቢ ነው።
ሀይቁ ለዓሣ ምርት፣ ለቱሪዝምና ለአካባቢው ሕዝብ አሳ በማስገር ኑሮውን የሚመራበት በመሆኑ ለብዙዎች መተዳደሪያ ባለውለታ ነው። በአርባ ምንጭ ከተማ ግርጌ በስፋት ተንጣለው የሚገኙት እነዚህ ሀይቆች ከተማዋን ውበት ከማጎናጸፍና ለቱሪስት መስህብ ከመሆኑ ባለፈ በብዛት አሳ የሚገኝባቸው ናቸው።
በአባያና ጫሞ ሀይቆች መካከል የሚገኘውና በተለምዶ “የእግዜር ድልድይ” ተብሎ የሚጠራውም በሁለቱ ሀይቆች መካከል ከነ ግርማ ሞገሱ የሚታይ አስደናቂ ስፍራ ነው። የእግዜር ድልድይም የአባያና ጫሞ ሀይቆችን የተፈጥሮ ውበት በዚሁ ስፍራ ላይ ሆኖ ለመመልከት የሚያስችል ነው።
ከዚህም በተጨማሪ በሁለቱ ሀይቆች ራስጌ ላይ የሚገኘውና የበርካታ የዱር እንስሳት መገኛ የሆነው የነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክ ሌላኛው የቱሪዝም መስህብ ነው። በአካባቢው የሚገኙ የተለያዩ እንስሳትና ዕፅዋት ለስፍራው ላቅ ያለ ድምቀትን ያላበሱ ናቸው። የነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክ፣ የአባያና ጫሞ ሐይቆች፣ የእግዜር ድልድይ እና ሌሎችም ተደምረው የአርባ ምንጭ ሃብትና የውበት መገለጫ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ። እውቁና ተወዳጁ አርቲስት አቡሌ “ኑደሬይ ጋሞ ጎፋ ኦይቻ አርባምንጬ ሚዚሪ ካልሲ የደስ አባያ ጫሞ ሞሌ” ያለውም ለዚሁ ነው።
አርባ ምንጭ ሀይቆቿን ጨምሮ የተፈጥሮ ሀብቶቿን በመንከባከብና በማልማት ውበቷን ብቻ ሳይሆን የልማት አቅሟንም የማሳየት መልካም እድል አላት። አሁን ላይ የሀይቆችን ዳርቻ ከአርባ ምንጭ ከተማ የኮሪደር ልማት ጋር በማሰናሰል በማልማት የተጀመረው ስራ ከተማዋን ይበልጥ የመስህብ ማእከል ለማድረግ የሚያስችል ነው።
የገበታ ለትውልድ ኢንሼቲቭ አካል የሆነውና በአባያ ሃይቅ ዳርቻ የተገነባው የአርባ ምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞሪትም ሌላው የከተማዋ የፈርጥ ሲሆን ከሀገር አልፎ ዓለም አቀፋዊ ጉባኤዎችን ለማስተናገድ የሚያስችል አቅም ማካበት አስችሏል።
የአባያና ጫሞ ሐይቆች በተፈጥሮ ውበታቸው፣ በውሃ ውስጥና ዙሪያ በሚገኙ የዱር እንስሳትና ወፎች እንዲሁም በመዝናኛ እሴታቸው ልዩ የቱሪዝም መዳረሻዎች ናቸው። የሐይቅ ዳርቻ የቱሪዝም ማዕከል መገንባት ዘመናዊ የአገልግሎት መስጫ የመረጃ ማዕከላትና የጎብኚዎች መቀበያ ስፍራዎች እንዲሁም በጋሞ ልማት ማህበር የተጀመሩ የጀልባ ጉዞ አገልግሎቶችን ማሳደግ እና ማስፋፋት አስፈላጊ ነው። ሐይቆቹን እንደ ተፈጥሯዊ ሀብት ብቻ ሳይሆን እንደ ስትራቴጂካዊ የኢኮኖሚ አቅም ማካበቻ በማድረግ ለዘላቂ ልማትና ተጠቃሚነት መትጋት ይገባል።