ቀጥታ፡

ታዳጊ ሀገራትን ከአደጋ ለመታደግ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ አቅርቦት በአስቸኳይ ማሳደግ ይገባል - የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 2/2019 (ኢዜአ)፦ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ፋይናንስ አቅርቦት በማሳደግ ታዳጊ ሀገራትን መደገፍ እንደሚገባ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ገለጹ።

ታዳጊ ሀገራት ወደ ንጹህ ኃይል የሚያደርጉትን ሽግግር እንዲያፋጥኑም ጠይቀዋል።

31ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በቱርኪዬ አንታሊያ እየተካሄደ ይገኛል።

“ጉዞ ወደ ዘላቂ፣ አይበገሬነት እና ፍትሃዊነት ወደተረጋገጠበት መጻኢ ዘመን” የጉባኤው መሪ ቃል ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር የበለጸጉ እና ከፍተኛ በካይ ጋዝ የሚለቁ ሀገራት የበከሉትን ያህል ካሳ በመክፈል ለታዳጊ ሀገራት የሚውል 1.3 ትሪሊዮን ዶላር የአየር ንብረት ፋይናንስ እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል።

እንዲሁም የዓለም አቀፍ የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀትን በየዓመቱ በስድስት በመቶ መቀነስ እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የአየር ንብረት ቀውሱ እየቀደመን ነው ያሉት ጉቴሬዝ፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊከሰት የሚችለውን አስከፊ አደጋ ለመግታት የሚያደርገው እንቅስቃሴ በጣም አዝጋሚ መሆኑን አመልክተዋል።

አሁን ያሉት ብሔራዊ የአየር ንብረት ቃልኪዳኖች ሙሉ በሙሉ ቢተገበሩ እንኳ በዓመት ከሚያስፈልገው የልቀት ቅነሳ መጠን አንድ ሶስተኛውን ብቻ ነው ማሳካት የሚችሉት ብለዋል።

አሁን ያለው አካሄድ ከቀጠለ እስከ ክፍለ ዘመኑ መጨረሻ የዓለም ሙቀት ከ2.5 ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ እንደሚጨምር የጠቆሙት ዋና ፀሐፊው፤ ይህም ሊመለሱ የማይችሉ አስከፊ የተፈጥሮ ቀውሶችን እንደሚያስከትል አስጠንቅቀዋል።

ዓለም ወደ ታዳሽ ኃይል የሚደረገውን ሽግግር ማፋጠን እና ተጋላጭ ማህበረሰቦችን ከአየር ንብረት አደጋዎች የመጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣም ነው ጥሪ ያቀረቡት ።

መንግሥታት ከቃልኪዳን አልፈው በተግባር የተደገፉ እርምጃዎችን እንዲወስዱ አሳስበዋል።

ዋና ፀሐፊው የበለጸጉና በካይ ጋዝ የሚለቁ ሀገራት ለአየር ንብረት ቀውሱ ተገቢውን ኃላፊነት እንዲወስዱ እና የታዳጊ ሀገራትን አቅም የሚያጠናክር የፋይናንስ ድጋፍ እንዲጨምሩ ጠይቀዋል።

በተጨማሪም መንግሥታት የነዳጅ ኩባንያዎች ከፍተኛ ትርፍ ላይ ታክስ በመጣል በአየር ንብረት ጉዳት ለደረሰባቸው ሀገራት ድጋፍ እንዲያውሉ አሳስበዋል።

በካዮች ተገቢውን ካሳ መክፈል አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል።

ታዳጊ ሀገራት ያለ ተጨማሪ የኢኮኖሚ ጫና ወደ ንጹህ ኃይል መሸጋገር እንዲችሉ፤ ተመጣጣኝ የፋይናንስ አቅርቦትን፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን፣ ጠንካራ የዝግጁነት እርምጃዎችን እና የተቀናጀ ዓለም አቀፍ ትብብርን ያካተተ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጉቴሬዝ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም