ቀጥታ፡

የተፈጥሮና የባህል ሀብት ምድር

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሲነሳ የኢትዮጵያዊያን የጋራ አሻራ ያረፈበት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መነሳቱ የማይቀር ነው። በክልሉ እምቅ የተፈጥሮ ሃብት፣ ጥብቅ ደኖች፣ የማእድን ሃብት፣ ባህላዊ እሴቶችና ሌሎችም እምቅ ሃብቶች ይገኛሉ።

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የተፈጠረው ሰፊው ሰው ሰራሽ ሃይቅ (የንጋት ሐይቅ) የአካባቢው ተጨማሪ ግርማ ሞገስ ሆኗል። ከ70 በላይ ደሴቶችን በውስጡ የያዘው ይህ ሃይቅ የአካባቢውን የቱሪዝም መስህብነት ከፍ የሚያደርግ ልዩ ገጸ በረከትም ሆኗል። በኃይቁ እየተመረተ ያለው የዓሣ ሃብት ለበርካታ ወጣቶች የሥራ እድል እየፈጠረ፣ የገቢ ምንጭና የምግብ ዋስትና መሰረት እየሆነ ይገኛል።


 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለው  እምቅ የወርቅ ሃብት የወርቅ ምድር  መሆኑም ይታወቃል። በተለይም በአባይ፣ በበለስና በዳቦስ ወንዞች ዙሪያ የባህላዊ የወርቅ ማውጣት ሥራዎች ይከናወናሉ። በወንዞች ዳርቻ የሚካሄደው የወርቅ ፍለጋና ማውጣት ሥራ ለበርካቶች የገቢ ምንጭ ሲሆን ከወርቅ በተጨማሪ እብነበረድ፣ መዳብና ሌሎችም ማዕድናት በብዛት ይገኛሉ።

ከአባይ ገባሮች መካከል አንዱ የሆነው (የዳቦስ) ወንዝም የክልሉ ህዝብ ሁነኛ የኢኮኖሚ መሰረት ሆኖ እያገለገለ መሆኑ ይታወቃል። የዳቦስ ወንዝ ለአካባቢው ህዝብ የእርሻ፣ የዓሣ ሀብትና የመስኖ ልማት ስራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑም ይታወቃል። የዳቦስ ወንዝን ጨምሮ የአባይና የበለስ ወንዞችም ለክልሉ ብሎም ለሀገር የልማት አቅም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው።


 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በኢትዮጵያ የቀርከሃ ሀብት በስፋት ከሚገኝባቸው አካባቢዎች መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳል። የቀርከሃ ደኖች የተፈጥሮ ውበት ከመሆናቸው ባሻገር ለአካባቢው ህዝብ የኑሮ መሠረትና የኢንዱስትሪ ግብዓት ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የዳበሩ የባህል መገለጫዎችና አስደናቂ ትእይንቶች ያሉበት መሆኑም ይታወቃል። ከእነዚህ ባህላዊ መገለጫዎች መካከል ዙምባራ የተባለው ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያ ልዩ መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል። የዙምባራን ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያ በደስታና በተለያዩ ማህበራዊ ዝግጅቶች ይጠቀሙበታል።


 

በክልሉ የሚገኘው ሰፊ ለም መሬት፣ የውሃ ሀብትና ምቹ የአየር ንብረት ለግብርና ልማትና ምርታማነት ትልቅ አቅም መሆኑ ይታወቃል። ሰሊጥ፣ ማሽላና ሌሎችም የግብርና ምርቶችና የንብ ማነብ ስራ በስፋት ይከናወናል።

በአጠቃላይ ክልሉ የኢትዮጵያውያን የጋራ አሻራ ያረፈበት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መገኛ፣ የንጋት ሃይቅ ውበት የተፈጠረበት፣ የወርቅ ምድር፣ የቀርከሃ ሃብት በብዛት የሚገኝበትና የዙምባራ ድምፅ ከፍ ብሎ የሚሰማበት መሆኑ ይታወቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም