ለሀገር ብሔራዊ ጥቅም መከበር የሁሉም ዜጋ የነቃ ተሳትፎ ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገር ብሔራዊ ጥቅም መከበር የሁሉም ዜጋ የነቃ ተሳትፎ ያስፈልጋል
ነገሌ ቦረና ፤ ህዳር 2/2019 (ኢዜአ) ፡- የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበርና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የዜጎች ያልተቆጠበ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን በደቡብ ኦሮሚያ ዞን የነገሌ ቦረና ከተማ ጡረተኛ መምህራንና የቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ገለጹ።
በከተማዋ "ዘላቂ ሰላምና ደኅንነት ለአረጋውያን መልካም ሕይወት" በሚል መሪ ሐሳብ የአረጋውያን ቀን ተከብሯል።
በበዓሉ ከተሳተፉት መካከል የቀድሞ የሠራዊት አባል ሐምሳ አለቃ ሐጂ አብዲ ሮባ እንደገለጹት፤ የሀገር ሉዓላዊነት ከትውልድ ወደ ትውልድ በአደራ የሚተላለፍ ከፍ ያለ እሴት ነው።
ብሔራዊ ጥቅም በዜጎች መስዋዕትነት የሚከበር መሆኑን የጠቀሱት ሐምሳ አለቃ ሐጂ፤ በታሪክ አጋጣሚ ያጣነውን የኢትዮጵያ የባሕር በር ለማስመለስ የመደመር መንግሥት እያደረገ ያለው ሁለንተናዊ ጥረት እጅግ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
ሌላኛው የከተማው ነዋሪና የሀገር ሽማግሌ ጡረተኛ መምህር ግርማ ኃይሌ በበኩላቸው፤ የባሕር በር የመኖርና ያለመኖር የህልውና ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ የታሪኳ አካል መሆኑን ጠቁመዋል።
ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ በመሆኑ፣ አዲሱ ትውልድ ይህንን ታሪካዊ መብት ለማስከበር ከመንግሥት ጎን መሰለፍ አለበት ሲሉም መክረዋል።
መንግሥት በፍትሐዊ የ"ሰጥቶ መቀበል" መርህ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር እያደረገ ያለው ጥረትና እየሄደበት ያለው ርቀት እጅግ የሚያስመሰግን መሆኑን ደግሞ ሌላው ጡረተኛ መምህር አበጀ ታፈሰ ገልጸዋል።
የነገሌ ቦረና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይ አቶ የሱፍ አብዱረህማን በበኩላቸው፤ ሰፊ ልምድ ያላቸውና የሀገር ባለውለታ የሆኑት አረጋውያን በማኅበር ተደራጅተው በሥራ ራሳቸውን እንዲደግፉ የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግላቸው አስታውቀዋል።
ለዚህም ማሳያ እንዲሆን የከተማ አስተዳደሩ ለአረጋውያኑ ማኅበር 850 ካሬ ሜትር የህንጻ መስሪያ ቦታ መስጠቱን ይፋ አድርገዋል።
ከዚህም ባለፈ አረጋውያኑ በሰላምና በልማት ሂደት ውስጥ ያላቸውን የነቃ ተሳትፎና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።