ቀድሞ በመመርመርና የአኗኗር ዘይቤን በማስተካከል የስኳር በሽታን መከላከል ይገባል -ዶክተር ጌታሁን ታረቀኝ - ኢዜአ አማርኛ
ቀድሞ በመመርመርና የአኗኗር ዘይቤን በማስተካከል የስኳር በሽታን መከላከል ይገባል -ዶክተር ጌታሁን ታረቀኝ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 3/2019 (ኢዜአ)፦ ቀድሞ በመመርመርና የአኗኗር ዘይቤን በማስተካከል የስኳር በሽታን መከላከል እንደሚገባ ተመለከተ።
የኢትዮጵያ የስኳር ሕመም ማህበር የዓለም የስኳር ሕመም ቀንን ምክንያት በማድረግ ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ለተውጣጡ ሙያተኞች ያዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ ስኳር ሕመም ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ጌታሁን ታረቀኝ በወቅቱ እንደገለጹት በስኳር በሽታ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው።
በተለይም በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በፍጥነትና በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
ለስኳር በሽታ አጋላጭ ከሆኑ መንስኤዎች መካከል የሰውነት ክብደት መጨመር፣ ትምባሆ ማጤስ፣ አልኮል አብዝቶ መጠጣትና የስኳር መጠናቸው የበዛ የፋብሪካ ምግቦችን አዘውትሮ መመገብ በዋናነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የስኳር ሕመም ለልብ፣ ለኩላሊት፣ ለደም ግፊትና ለሌሎች ሕመሞች እንዲሁም ለሞት እንደሚዳርግ ጠቁመው፣ በተለይም ለእግር መቆረጥ፣ ለዓይን እይታ ማነስ እና ለልብ ሕመም ከሚያጋልጡ መንስኤዎች መካከል በአንደኛ ደረጃ እንደሚቀመጥ አመልክተዋል።
የሽንት መብዛት፣ የሰውነት ክብደት መቀነስ፣ ከፍተኛ የውሀ ጥምና የድካም ስሜት መኖር የበሽታው ምልክቶች መሆናቸውን ጠቁመው፣ በሽታው ምንም ምልክት ሳያሳይ የሚቆይበት ሁኔታ እንዳለም ጠቁመዋል።
በመሆኑም ቀድሞ በመመርመርና የአኗኗር ዘይቤን በማስተካከል በሽታውን መከላከል ይገባል ያሉት ዶክተር ጌታሁን፣ በተለይ ተመርምሮ እራስን በማወቅ አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ በሽታውን በ80 በመቶ መከላከል ያስችላል ብለዋል።
በሽታው እንዳለ በምርመራ ቢታወቅ እንኳ አመጋገብን ጨምሮ የአኗኗር ዘይቤን በማስተካከል፣ በሕክምናና በአካል ብቃት እንቅስቃሴ የበሽታውን መጠን መቀልበስ እንደሚቻል አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ስኳር ሕመም ማህበር ላለፉት 40 ዓመታት አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጠቁመው፣ በአሁኑ ወቅትም ማህበሩ በመላ ሀገሪቱ በ96 ቅርንጫፎች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።
በዋናነትም የስኳር ሕክምናን በማሻሻል፣ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመስጠት፣ ለዘርፉ ሙያተኞች ስልጠና መስጠት፣ የጤና ተቋማትን በመድሀኒትና በህክምና ቁሳቁስ በመደገፍ እና ለፖሊሲ የሚሆኑ ሀሳቦችን በማመንጨት ላይ አተኩሮ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ማህበሩ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ 54 ሆስፒታሎች ለ20 ሺህ የስኳር ሕሙማን ህጻናት እያደረገ ያለውን የኢንሱሊን አቅርቦት ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠሉን ለአብነት ጠቅሰዋል።
የሚዲያ ተቋማት ስለበሽታውና መደረግ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በማስጨበጥ ሀላፊነታቸውን በበለጠ እንዲወጡም ጠይቀዋል።
የዘንድሮውን የዓለም የስኳር ሕመም ቀንን ህዳር 5 ቀን 2019 ዓ.ም "ስኳር ሕመም አስቀድመን እርምጃ እንውሰድ" በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚከበርም አስታውቀዋል።