ቀጥታ፡

የሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል በአፈር አጠቃቀምና እንክብካቤ ላይ የተለያዩ ምርምሮችን እያካሄደ ነው

ሆለታ፣ ህዳር 2/2019 (ኢዜአ)፡- የሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል በአፈር አጠቃቀምና እንክብካቤ ላይ የተለያዩ ምርምሮችን እያካሄደ መሆኑን ገለጸ።

በሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል የአፈር ለምነት ተመራማሪ አቶ ዘለቀ ኦብሳ  እንዳሉት፤ ሆለታ ግብርና ምርምር በኮትቻ አፈር ምርምር ላይ የረጅም ጊዜ ልምድ ያለው ነው።

በዚህም ኮትቻ አፈር በዝናብ ጊዜ ውሃን በብዛት መያዝ እና በበጋ ወቅት በስፋት መሰነጣጠቅ ዋነኛ ችግር መሆኑን በመለየት እንደ አፈር ማጠንፈፍ የመሳሰሉ መፍትሔዎችን ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።


 

በአሁኑ ወቅት  እንደ ሀገር አሳሳቢ የሆነው የአፈር መሸርሸርን ለመታደግ በአፈር አጠቃቀምና እንክብካቤ ዙሪያ ሰፋፊ የጥናት ስራዎችን በማካሄድ ላይ ይገኛል ብለዋል።

በተለይም ከህዝብ ቁጥር መጨመርና ከአጠቃቀም ጉድለት የተነሳ ከፍተኛ የአፈር መሸርሸር ስለሚኖር ለዚህ መፍትሔ የሚሆኑ ውጤቶችን ለማምጣት ተግቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በአፈርና ውሃ ምርምር ስር ስድስት የትኩረት መስኮች አሉት። እነዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ በማዕከሉ አስተባባሪነት የሚካሄደው የአፈር አሲዳማንት ምርምር፣ በአፈር ለምነት ላይ የሚካሄድ ምርምር፣ የተፋሰስ ልማት፣ የኮትቻ አፈር ጥናት እና የተፈጥሮና ማዳበሪያ ዝግጅት ላይ የሚካሄዱ ምርምሮችን እንደ አብነት አንስተዋል።

ማዕከሉ ደረጃውን የጠበቀ የአፈር፣ የእፅዋትና የውሃ ምርምር ላቦራቶሪዎች እንዳሉት አንስተው በዚህም የምርምር ውጤቶቹን ለዩኒቨርሲቲዎች እና ለአርሶ አደሮች በመስጠት ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ለአብነትም ቀደም ሲል በውል የማይታወቀው የአፈር አሲዳማነት ችግር በአሁኑ ጊዜ ችግሩ በምርምር ተለይቶ አፈሩን በማከምና የእርሻ ስራውን በማስተካከል ምርትና ምርታማነት መጨመር መቻሉን እንደ ምርምር ውጤታቸው አንስተዋል።

አፈርን በኖራ ከማከም ባለፈ አሲዳማ አፈር ተቋቁመው የተሻለ ምርት መስጠት የሚችሉ የሰብል ዝርያዎችም በምርምር ተገኝተው ለአርሶ አደሮች በመስጠት ውጤት ማስገኘታቸውን አንስተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም