ቀጥታ፡

መደመር የአፍሪካን ብልፅግና የሚያረጋግጥ የተሰናሰለ አቅም የሚገነባ ፍልስፍና ነው - የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች

አዲስ አበባ፤ ህዳር 2/2019 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የመደመር ፍልስፍና የአፍሪካን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ የተሰናሰለ አቅም በመገንባት ለጋራ ዓላማ መነሳሳትን የሚፈጥር መሆኑን የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ገለጹ።

ሁለተኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ "ዕድገትን መምራት ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ የአፍሪካ መጻኢ ኢኮኖሚ መሃንዲሶች" በሚል መሪ ሀሳብ ከጥቅምት 26 እስከ 28 ቀን 2019 ዓ.ም ተካሂዷል።

በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ በተካሄደው ጉባዔ ከ54 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ 1 ሺህ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ ባለድርሻ አካላትና ተጋባዥ እንግዶች ተሳትፈዋል።

የጉባዔው ተሳታፊ የአፍሪካ ሀገራት የፓርቲ ተወካዮች ለኢዜአ እንዳሉት፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫ ፉክክር ባለፈ ለሀገራዊ ሽግግር ውጤታማነት አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይገባል።

የዑጋንዳ ፓርላማ አባልና የቀድሞ የተቃዋሚ ፓርቲዎች መሪ አኦል ቤቲ ኦካን፤ ኢትዮጵያ የወጣቶችና ሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ በማላቅ በአስደናቂ የልማት ጎዳና ላይ መሆኗን አዲስ አበባ ማሳያ ናት ብለዋል።

የመደመር ፍልስፍና ያስመዘገበው አስደማሚ የልማት ስኬትም የአፍሪካ ሀገራትን ዕድገት ለማሳለጥ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ እንደሆነ ተናግረዋል።

መደመር አፍሪካውያንን ለጋራ ዓላማ ለማነሳሳት ጉልህ ፋይዳ ያለው ፍልስፍና መሆኑን፤ ፍልስፍናውንም በሚገባ በመገንዘብ አህጉራዊ ዕድገትን የሚያሳልጥ የጋራ አረዳድ መያዝ ያስፈልጋል ብለዋል።

የአህጉሪቷ አባል ሀገራት የፖለቲካ ፓርቲዎችም ከምርጫ ፉክክር ባለፈ ለሀገራዊ ልማት በመስራት ሕገ መንግሥታዊ መርህን በማክበር ለዜጎች ሕይወት መሻሻል መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የመደመር ፍልስፍናን የተሰናሰለ አቅም የመገንባት ከኢትዮጵያ በመጋራት የአህጉራችን መጻኢ ዕድል ለመወሰን መትጋት ይኖርብናል ብለዋል።


 

ከማላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሬጅስትራር ጽሕፈት ቤት የመጡት ኤደን ምዙማራ በበኩላቸው፤ መደመር የልማት ዓላማዎችን ለማሳካት የዘርፎችን ትብብር የሚያጠናክር ፍልስፍና መሆኑን ተገንዝቢያለሁ ብለዋል።

ፍልስፍናው ትብብርን በማጠናከር ቅልጥፍናን እንደሚያመጣና የአፍሪካ አገራት የኢኮኖሚ ልማታቸውን እንዲያራምዱ ሊያግዝ እንደሚችል ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለው የመሠረተ ልማትና ሌሎች የልማት ሥራዎች ለአፍሪካ ሀገራት ትምህርት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም