የታላላቅ አትሌቶች የጽናት እና የስኬት መንገድ ለታዳጊዎች ትልቅ የርዕይ ምንጭ ሆኗል - ኢዜአ አማርኛ
የታላላቅ አትሌቶች የጽናት እና የስኬት መንገድ ለታዳጊዎች ትልቅ የርዕይ ምንጭ ሆኗል
የኢትዮጵያን የሁልጊዜም ታላቅነትና ክብር በዓለም አቀፍ የስፖርት መድረክ ከፍ አድርገው ያስጠሩ ታላላቅ አትሌቶች ያለፉበት የስኬት መንገድ ለታዳጊዎችና ወጣቶች ትልቅ የርዕይ ምንጭ መሆኑን በዘርፉ በመሰልጠን ላይ የሚገኙ ወጣት አትሌቶች ተናገሩ።
የኢትዮጵያን ስም በዓለም የስፖርት መድረክ ከፍ አድርገው ያስጠሩ ታላላቅ አትሌቶች የስኬት ታሪክ የዛሬ ብቻ ሳይሆን የመጪው ትውልድ ኩራት እና የተነሳሽነት ምንጭ ነው።
የሀገራችንን ሰንደቅ ዓላማ በድል ያውለበለቡት ቀደምት የሀገር ጀግኖች በትውልዱ ልብ ውስጥ የማይሽር ቦታ ይዘዋል።
እነዚህ የድል ተምሳሌቶች በላባቸው፣ በትጋታቸው፣ በጽናታቸውና ለሀገራቸው ባላቸው ፍቅር የኢትዮጵያን ታላቅነት ለዓለም ከማሳየት ባለፈ፣ የሀገር ፍቅር በተግባር ሲገለጽ ምን ያህል ታሪክ እንደሚሠራ ያስመሰከሩ ናቸው።
ስማቸው በድል ታሪክ ውስጥ ብቻ የተቀመጠ ሳይሆን፣ በአዲሱ ትውልድ ልብ ውስጥ የኩራትና የመነሳሳት ምንጭ ናቸው።
ትውልዱ ለሀገሩ የኢትዮጵያን ታላቅ ታሪክና የወደፊት አቅም እያሰበ ከዚያ ታላቅነት ጋር የሚመጣጠን ራዕይ እንዲሰንቅ የሞራል ስንቅ የሚሆኑ የትውልድ አርአያዎች ናቸው።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የነገ ተስፋዎች፣ የቀደሙት አትሌቶች ያስመዘገቡት ውጤትና ለሀገራቸው ያበረከቱት አስተዋፅኦ ትልቅ የሞራል ስንቅ መሆኑን ገልጸዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል ሰልጣኝ ላምሮት ወልዴ ፣ በአትሌቶች መፍለቂያነት ከምትታወቀው በቆጂ መወለዷና ማደጓ ለአትሌቲክስ ልዩ ፍቅር እንዲያድርባትና ወደ ስፖርቱ እንድትቀላቀል እንዳነሳሳት ገልጻለች።
በአካዳሚው በምታገኘው ዕውቀት፣ ክህሎትና ልምድ በመታገዝ ከእሷ በፊት የነበሩ ታላላቅ አትሌቶች የሠሩትን አኩሪ ታሪክ ለማስቀጠል እየተጋች እንደሆነም ጠቁማለች።
የወደፊት ዓላማዋም በአትሌቲክሱ ዘርፍ የማይረሳ ታሪክ መጻፍ መሆኑን ተናግራለች።
ከሻሸመኔ የመጣውና በአካዳሚው ሰልጣኝ አብዱልሀሚድ ቱሉ በበኩሉ፣ በአካባቢው አትሌቲክስን የሚያሰለጥኑ ክለቦች መኖራቸውና በተማረበት ትምህርት ቤት ስፖርታዊ ውድድሮች የሚካሄዱበት ምቹ ሁኔታ መኖሩ ወደ ሩጫው ዓለም እንዲገባ አድርጎኛል ብሏል።
ወደ ኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ መቀላቀሉም ብቁ አትሌት ለመሆን የሚያግዙትን ልምዶች እንዲያገኝ እድል እንደፈጠረለት አስረድቷል።
ወደፊትም እንደ ቀደሙት ጀግኖች አትሌቶች በዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ኢትዮጵያን በመወከል ለሀገሩ ሜዳሊያ ለማምጣት ዓላማ መሰነቁን ተናግሯል።
ከአርሲ የመጣው የአካዳሚው ሰልጣኝ ቀነኒሳ ተሾመ፣ በሀገራችን ያሉ ታዋቂ አትሌቶች ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ሀገራቸውን ማስጠራታቸው፣ ባገኙት ትልቅ ዝና እና ገቢ የራሳቸውንም ሆነ የሀገራቸውን ሕይወት ሲቀይሩ እያየ ማደጉን ገልጿል።
ይህም ወደ አትሌቲክሱ እንዲሳብ ትልቅ መነሳሳት እንደፈጠረለት አብራርቷል።
ውጤታማነት በቀላሉ እንደማይገኝ በመገንዘብም የነገ ስመጥር አትሌት የመሆን ህልሙን ለማሳካት በቁርጠኝነት እንደሚሠራም ገልጿል።
ከአርባምንጭ የመጣችውና የሦስተኛ ዓመት የአትሌቲክስ ሰልጣኝ የሆነችው መክብብ ማናዬም፣ በተለይም ሴት አትሌቶች በዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ድል ሲቀዳጁና ለሀገራቸው ኩራት ሲሆኑ መመልከቷን አንስታለች።
በነገው ለሀገሯ ኩራት የምትሆን አትሌት ለመሆን በአካዳሚው የሚሰጡ ስልጠናዎችን በትጋት እየተከታተለች መሆኑን ገልጻለች።
በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የአጭር ርቀት መሰናክል ሩጫ አሰልጣኝ ጎሳ ሞላ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ከምትታወቅባቸው የስፖርት ዓይነቶች አንዱ በሆነው አትሌቲክስ ዘርፍ ብቁና ውጤታማ አትሌቶችን ለማፍራት በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
የሀገሪቱን የአትሌቲክስ ታሪክ የቀየሩና በዓለም መድረክ ውጤታማ የሆኑ አትሌቶች ያለፉበትን መንገድና የደረሱበትን የስኬት ደረጃ ለሰልጣኞች በማስረዳት ተመሳሳይ የስኬት ህልም እንዲሰንቁና ጠንካራ የሥነ ልቦና ዝግጅት እንዲኖራቸው ይደረጋል ብለዋል።
የአካዳሚው የአትሌቶች ትምህርትና ስልጠና መሪ ሥራ አስፈጻሚ መሪ ኢንስትራክተር ፍቃዱ ከበደ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ዘርፍ ለውጤታማነት የሚያግዙ በርካታ ተፈጥሯዊ ሀብቶችና ምቹ ሁኔታዎች ያሏት ሀገር ናት።
እነዚህን ምቹ ሁኔታዎች በመጠቀም ለዘመናት በርካታ አትሌቶች የሀገሪቱን ስም በዓለም መድረክ ከፍ ከማድረግ ባለፈ፣ ለኢትዮጵያ ገጽታ ግንባታና ለኢኮኖሚ ዕድገትም ጉልህ አስተዋፅኦ ሲያበረክቱ መቆየታቸውን አንስተዋል።
የአትሌቲክሱን ገናና ስም ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስቀጠል መንሥት ለአካዳሚው ትኩረት በመስጠቱ ታዳጊ አትሌቶችን የማፍራት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።