ቀጥታ፡

በደቡብ ወሎ ዞን በተያዘው የበጋ ወራት የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ይከናወናል

ደሴ፤ ህዳር 2/2019 (ኢዜአ)፡-በደቡብ ወሎ ዞን በተያዘው የበጋ ወራት በ43 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ እንደሚከናወን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ አህመድ ጋሎ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ የበጋ ወራት የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ በተሻለ እና ዘላቂነት ባለው መንገድ እየተከናወነ ይገኛል።

ባለፉት ዓመታትም የደን ሽፋን በማሳደግ፣ ምርታማነትን በመጨመር፣ የሥራ ዕድል በመፍጠርና የሕፃናትና የእንስሳት መኖ በቀላሉ እንዲገኝ በማድረግ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል ነው ያሉት።

በዘንድሮው የበጋ ወቅትም በ43 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ለማከናወን የግንዛቤ ፈጠራ፣ የመስሪያ ቁሳቁስ ልየታ፣ የባለሙያዎች ስልጠናና ሌሎች ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን አብራርተዋል።

የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራው በተያዘው ወር ለመጀመር ታቅዶ እየተሰራ ሲሆን፣ ከ600 ሺህ በላይ ሕዝብ እንደሚሳተፍ ገልጸዋል።

የተሁለደሬ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድ ጋሻው በበኩላቸው፤ ካለፉት አመታት ልምድ በመነሳት የዘንድሮውን ዓመት የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ  ውጤታማ ለማድረግ ዝግጅት አድርገናል ብለዋል።

ሕብረተሰቡን አስተባብሮ ልማቱን ከማከናወን ባለፈ፣ በለሙ አካባቢዎች አትክልትና ፍራፍሬዎችን  በማልማት ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችል አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

"የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ያለውን ጠቀሜታ በተግባር በማየታችን ልማቱን በተነሳሽነት እያከናወን እንገኛለን" ያሉት ደግሞ በደሴ ዙሪያ ወረዳ የ025 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አራጋው ዘውዱ ናቸው።

በዘንድሮው ዓመትም በተራራማ አካባቢዎች፣ በማሳቸውና በሌሎችም የተራቆቱ መሬቶች ላይ ልማቱን ለማከናወን መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በአርጎባ ብሔረሰብ አስተዳደር ልዩ ወረዳ የ01 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሰይድ የሱፍ በበኩላቸው፤ ቀደም ሲል በተከናወኑ የልማት ሥራዎች የተራቆቱ አካባቢዎች መልሰው ማገገም መቻላቸውን ነው የሚናገሩት።

በዘንድሮው ዓመትም የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል በማሳና በተራራ ላይ እርከኖችን ለመስራት መዘጋጀታቸውንም ነው የተናገሩት።

በደቡብ ወሎ ዞን የዘንድሮው የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ በ1 ሺህ 400 ተፋሰሶች ላይ እንደሚከናወን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም