ቀጥታ፡

በምስራቅ ጎጃም ዞን ከ34 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ እየለማ ነው

ደብረ ማርቆስ፣ ህዳር 2/2019 (ኢዜአ)፡- በምስራቅ ጎጃም ዞን ከ34 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ እየለማ መሆኑ ተገለጸ።

በመምሪያው የመስኖ ልማት ባለሙያ አቶ ካሳሁን ዘለቀ ለኢዜአ እንደተናገሩት፣ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ ምርቱን ለውጭ ገበያ የማቅረብ ግብ ተይዞ እየተሠራ ነው።

የበጋ ወራት ስንዴ ልማት ምርታማነትን ለማሳደግ ለተሳታፊ አርሶ አደሮች ሥልጠና ከመስጠት ባሻገር የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

ለአርሶ አደሮቹ የተሻሻሉ የስንዴ ዝርያዎችና የማዳበሪያ ግብዓት በወቅቱ እየቀረበላቸው እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ ከሚለማው መሬት ውስጥም 90 በመቶ የሚሆነው በኩታ ገጠም እንደሚለማ ገልጸዋል።

እስካሁን በተካሄደው ጥረትም ከ34 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ማልማት መቻሉን ገልጸው፣ ዕቅዱን በተሟላ መንገድ ለማሳካትም ጥረቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል። 

በበጋ መስኖ ስንዴ ከሚለማው መሬትም ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ አስረድተዋል።

በዞኑ ባለፈው ዓመት በበጋ ወራት በመስኖ ከለማው ስንዴ 1 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ምርት መሰብሰቡም ተጠቁሟል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም