ቀጥታ፡

በዞኑ የተከናወነው የኬሚካል ርጭትና የአጎበር ስርጭት የወባ ተጋላጭነትን ቀንሷል

ገንዳ ውኃ፣ ህዳር 2/2019  (ኢዜአ):-በምዕራብ ጎንደር ዞን የተከናወነው የኬሚካል ርጭትና የአጎበር ስርጭት የወባ ተጋላጭነትን በእጅጉ መቀነሱን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታወቀ።

የዞኑ ጤና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ዮሴፍ ጉርባ እንደገለጹት፤ ወባን ለመከላከል ሕብረተሰቡን ያሳተፈና በሳይንሳዊ መንገድ የተደገፈ ሰፊ ሥራ ተሠርቷል።

በዞኑ የተከናወነው የኬሚካል ርጭትና የአጎበር ስርጭት ሥራዎች የወባ ተጋላጭነትን በእጅጉ መቀነሳቸውን ገልጸው፤ ''አሁንም የቅድመ መከላከል ሥራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን" ብለዋል።

በወባ ትንኝ መራቢያ አካባቢዎችና ከፍተኛ ተጋላጭነት ባላቸው ቦታዎች ከ81 ሺህ በላይ መኖሪያ ቤቶችን ኬሚካል በመርጨት 227 ሺህ የሚሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ከበሽታው መጠበቅ እንደተቻለም አስረድተዋል።

እንዲሁም 70 ሺህ የሚጠጋ አጎበር ማሰራጨት መቻሉን ጠቅሰው፣ በዚህም በበሽታው የሚጠቁ ሰዎችን ቁጥር በመቀነስ ተጨባጭ ለውጥ ተገኝቷል ብለዋል።

በመተማ ጠቅላላ ሆስፒታል የማኅበረሰብ ጤና አደጋዎችና ወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጠር ኦፊሰር አቶ አንተነህ ገበየሁ በበኩላቸው፣ ለሕብረተሰቡ በተከታታይ የተሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱን ጠቁመዋል። 

የጤና ተቋማትና የሕብረተሰብ ጤና ባለሙያዎች ያደረጉት ርብርብ በሽታው ሊያደርስ የሚችለውን የጉዳት መጠን ለመቀነስ እንዳስቻለም ገልጸዋል።

የገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪ አቶ አየልኝ ይሁኔ በሰጡት አስተያየት፣ በሽታውን ለመከላከል የተካሄደው የኬሚካል ርጭትና የአጎበር ስርጭት ከበሽታው ለመጠበቅ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል። 

አሁን ላይ በወባ በሽታ የመያዝ ስጋታቸው መቀነሱን አንስተው፣ በቀጣይም ተግባሩ የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።

የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን የግንዛቤ ምክረ ሃሳቦች በመተግበር ማኅበረሰቡ ለወባ መከላከል ሥራዎች ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን የገለጹት ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ የኑስ አህመድ ናቸው።

"የተሰራጨው አጎበርና የኬሚካል ርጭት በአካባቢያችን ያለውን የወባ ጫና በእጅጉ እንዲቀንስ አድርጎታል፤ በቀጣይም ጥንቃቄዎቻችንን እናጠናክራለን" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም