ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የልማት ጥረት ለማሰናከል በግብጽ በኩል የሚሸረብ ሴራና በበላይነት ጠቅልሎ የመያዝ እሳቤ አብቅቶለታል

ሀዋሳ፤ ሕዳር 2/2019 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያን የልማት ጥረት ለማሰናከል በግብጽ በኩል የሚሸረብ ሴራና በበላይነት ጠቅልሎ የመያዝ የቅኝ ግዛት እሳቤ ያበቃለት ጉዳይ መሆኑን የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ መሁራን ገለጹ።

ኢትዮጵያ በውጭና በውስጥ የገጠማትን ጫና በመቋቋም በዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ ገንብታ በማጠናቀቅ የኃይል ልማቷን ማሳካት ችላለች።

የዓባይ ወንዝ የኤሌክትሪክ ኃይል አመንጭቶና ዓሣ አምርቶ ለጎረቤት አገራትም የኃይል ምንጭ በመሆን የቀጣናዊ የልማት ትስስር መሰረት ሆኗል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የተቋጨና ወደ ሥራ የገባ የልማት ፕሮጀክት መሆኑ ቢታወቀም የግብጽ የማደናገርና የሴራ ፖለቲካ ግን ዛሬም ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ከዚሁ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን፤ የኢትዮጵያን ልማትና የሀብቷን ተጠቃሚነት ለማሰናከል በግብጽ በኩል የሚሸረብ ሴራና ጠቅልሎ የመያዝ የቅኝ ግዛት እሳቤ ያበቃለት ጉዳይ ስለመሆኑ አንስተዋል።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጂኦግራፊና አካባቢ ጥናት ትምህርት ክፍል መምህርና ከፍተኛ ተመራማሪ ምስራቅ ታምሬ (ዶ/ር)፤ በኢትዮጵያ ላይ የግብጽ ጠላትነት ከጥንት እስካሁንም ያለማቋረጥ የዘለቀ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ልማት፣ እድገትና ተጠቃሚነቷ የማይመቻቸው የግብጽ ፖለቲከኞች በዓባይ ጉዳይ ላይ የተሸነፈ ሃሳብ ይዘው ህዝባቸውን ማደናገራቸውን ቀጥለውበታል ብለዋል።

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያን ልማትና የሀብቷን ተጠቃሚነት ለማሰናከል በግብጽ በኩል የሚሸረብ ሴራና ሀብቱን በበላይነት ጠቅሎ የመጠቀም የቅኝ ግዛት እሳቤ ያበቃለት ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል።

በውሃ አጠቃቀም ላይ ያላት ፖሊሲ ከዘመኑ ጋር ስለማይሄድና በትነት ብክነትን እያስከተለ በመሆኑ ማሻሻል እንዳለባትም መምህርና ከፍተኛ ተመራማሪው መክረዋል።

የኢትዮጵያ የህልውና መሰረት በሆኑት ሁለቱ ውሃዎች (ዓባይ እና ቀይ ባህር) ላይ ልማትና ተጠቃሚነት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ምስራቅ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

በዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተርና የስምጥ ሸለቆ ጥናትና ምርምር ማዕከል ተመራማሪ ፕሮፈሰር ምህረት ደናንቶ በበኩላቸው፤ የግብጽ የዘወትር ዓላማ የጋራ ልማትና ተጠቃሚነት ሳይሆን የኢትዮጵያን ልማት የማደናቀፍ መጥፎ እሳቤ መሆኑን አንስተዋል።

በከርሰ ምድር እና በሰው ሰራሽ ኃይቆች ግብጽ እምቅ የውሃ ሃብት እንዳላት እየታወቀ በኢትዮጵያ ላይ የምታራምደው የተሳሳተ ትርክት በፍፁም ተገቢነት የሌለው መሆኑን ተናግረዋል።

የኑቢያን አኩውፈር እና በአስዋን ግድብ ላይ የተሰራው የናስር ሰው ሰራሽ ሐይቅ ጨምሮ የከርሰ ምድርና ገጸ ምድር የውሃ ሃብት ያላት ግብጽ የዓባይን ውሃ አያያዝና አስተዳደሯ ደካማ ስለመሆኑም ገልጸዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን በማልማት ከራሷ አልፎ ቀጣናዊ የልማት ትስስር ለመፍጠር የምታደርገው ጥረት ሊነቀፍ ሳይሆን ሊደገፍ የሚገባው መልካም ተግባር መሆኑን ምሁራኑ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም