ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ31ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ ያነሷቸው ነጥቦች - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ31ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ ያነሷቸው ነጥቦች
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ31ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 31) ላይ ባደረጉት ንግግር ያነሷቸው ሀሳቦች :
- በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ እርምጃ ብቻውን ተነጥሎ የሚታይ ሳይሆን የአገሪቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አካል ነው።
- የኢትዮጵያ 90 በመቶ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ከውሃ የሚመንጭ መሆኑን እና ይህን ንጹህ ኃይል ለጎረቤት ሀገራትም ጭምር ታቀርባለች።
- በመደመር ፍልስፍና መሪነት እስካሁን ከ56 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል፣ ይህም የመሬት መበላሸትን ከመግታት ባለፈ ለዜጎች የሥራ እድል ፈጥሯል።
- በከተሞች የጎርፍ መከላከያዎችን ከመገንባት ባለፈ፣ የቆሸሹ ወንዞችን በማጽዳት ዳርቻዎቻቸውን ለቤተሰብና ህፃናት መዝናኛ ወደሆኑ መናፈሻዎች መቀየር ተችሏል።
- በድርቅ ወቅት በኢኮኖሚው ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ከውሃ፣ ከነፋስ፣ ከፀሐይ እና ከጂኦተርማል በተጨማሪ በኒውክሌር ኃይል ልማት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው።
- የአየር ንብረት አደጋዎችን አስቀድሞ ለመተንበይ የሳተላይት መረጃዎችን እና የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) በመጠቀም ለአርሶ አደሮች የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃ እየቀረበ ሲሆን፣ እርዳታዎችን በፍጥነት ለማድረስ የ"ፋይዳ" ዲጂታል መታወቂያ እያገዘ ይገኛል።
- ኢትዮጵያ የበካይ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ የነዳጅ እና ዲዚል ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር ማስገባት በመከልከል ሙሉ በሙሉ ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች (EV) የመሸጋገር እርምጃ ወስዳለች።
- ታዳጊ ሀገራት በየዓመቱ ለዕዳ ወለድ ብቻ ወደ 1 ትሪሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ይከፍላሉ። ይህም ከፍተኛ የብድር ወጪ የአየር ንብረት መቋቋም አቅማቸውን በመገደቡ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የብድር መመሪያዎቻቸውን ማሻሻል ይኖርባቸዋል።
- ኢትዮጵያ የኮፕ 32 ጉባኤን በምታስተናግድበት ወቅት፣ የአየር ንብረት ፋይናንስ ቃል ኪዳኖች ምን ያህል? እስከ መቼ? በምን አሰራር? ለሚሉት ሦስት ጥያቄዎች ግልጽ ምላሽ የሚሰጡበትን እና የቅድመ-አደጋ ዝግጁነት እርምጃዎችን የትኩረቷ ማዕከል አድርጋ ትሰራለች።
- ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2027 የሚካሄደውን የኮፕ 32 የአየር ንብረት ጉባኤ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ የምታስተናግድ በመሆኑ፣ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና ልዑካን ወደ ሰው ዘር መገኛ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ጥሪዬን አቀርባለሁ።