በአማራ ክልል ባለፉት ሁለት ወራት ከ14 ሺህ 500 ቶን በላይ የማር ምርት ተሰብሰቧል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ባለፉት ሁለት ወራት ከ14 ሺህ 500 ቶን በላይ የማር ምርት ተሰብሰቧል
ባህር ዳር፤ ህዳር 2/2019(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በሌማት ትሩፋት እየተነቃቃ በመጣው የንብ ማነብ እንቅስቃሴ ባለፉት ሁለት ወራት ከ14 ሺህ 500 ቶን በላይ የማር ምርት መሰብሰብ መቻሉን የክልሉ እንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ቢሮ ገለጸ።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚውና በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ከሚጠቀሱት ዋና ዋና የማርና ሰም አምራች አገራት አንዷ ስትሆን፣ የአማራ ክልል ደግሞ ለንብ ማነብ ሥራ ተስማሚ የሆነ ሥነ-ምህዳርና ሰፊ የዕፅዋት ሽፋን ካላቸው አካባቢዎች መካከል ይገኛል።
ይሁን እንጂ ዘርፉ ለብዙ ዓመታት በባህላዊ የአመራረት ዘዴ የተወሰነ በመሆኑ ካለው አቅም አንጻር በቂ ምርት ሳይገኝበት ቆይቷል።
ይህን ክፍተት ለመሙላትና የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የተጀመረው አገር አቀፉ "የሌማት ትሩፋት" መርሃ-ግብር፡ በንብ ማነብ፣ በወተት፣ በዶሮና በስጋ ምርት ላይ ትኩረት አድርጎ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።
የመርሃ-ግብሩ ዋና ዓላማ አርሶ አደሮች ዘመናዊ የንብ ቀፎዎችንና ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙ ማድረግ፣ የንብ ቀፎ ቁጥርን ማሳደግ፣ የጥራት ቁጥጥርን ማሻሻልና አምራቹን ከገበያ ጋር ማገናኘት ነው።
በክልሉ እንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ቢሮ አስተባባሪነት የተከናወኑት እነዚህ የቴክኒክና የአሰራር ማሻሻያዎች፣ በርካታ አርሶ አደሮችና ወጣቶች ወደ ዘርፉ እንዲገቡ ማስቻላቸው ተገልጿል።
ባለፉት ሁለት ወራት የተመዘገበው ከ14 ሺህ 500 ቶን በላይ የማር ምርት፣ የአካባቢውን ህብረተሰብ ገቢ ከማሳደጉም በላይ ለአገር ውስጥ ገበያና ለውጭ ኤክስፖርት የሚሆን የማር አቅርቦትን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ አለው።
በቢሮው የንብ ሀብት ልማት ባለሙያ መሐመድ ጌታሁን ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በክልሉ በዚህ ዓመት ከ40 ሺህ ቶን በላይ የማር ምርት ለመሰብሰብ የሚያስችል ስራ እየተሰራ ይገኛል።
በዚህም ባለፉት ሁለት ወራት በተደረገ ጥረት የእቅዱን 36 በመቶ ምርት መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም የማር ምርቱን የመሰብሰብ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልፀዋል።
የማር ምርቱ እየተሰበሰበ ያለው ከ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ ዘመናዊ፣ ሽግግርና ባህላዊ የንብ መንጋ የተሞሉ ቀፎዎች እንደሆነ ጠቅሰው፤ በንብ ማነብ ስራውም ከ547 ሺህ 900 በላይ ሰዎች እየተሳተፉ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በክልሉ ለንብ ማነብ ስራ እቅስቃሴ የሌማት ትሩፋት ከፍተኛ መነቃቃት መፍጠሩን ጠቅሰው፤ በዚህም በዘርፉ የተሰማሩ ወገኖችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያሳደግ መምጣቱን ገልፀዋል።
በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ጓጉሳ ሽኩዳድ ወረዳ ጅባይታ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ስለሺ አረጋ እንደገለጹት፤ ከ150 በላይ ዘመናዊና ባህላዊ ቀፎዎች 500 ኪሎ ግራም የማር ምርት ለማግኘት እየሰሩ ይገኛሉ።
በአሁኑ ወቅትም የማር ምርቱን የመሰብሰብ ስራ እየሰሩ ሲሆን በአካባቢው ወቅታዊ ገበያ 1 ኪሎ ማር 1ሺህ 200 ብር እየተሸጠ እንደሚገኝና ይህም ተጠቃሚነታቸውን እያሳደገው መሆኑን ገልፀዋል።
ባለፈው ዓመት ካመረቱት የማር ምርት ሽያጭ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ማግኘት እንደቻሉም አስታውሰዋል።
በዚህ ዓመት 215 ከሚሆኑ በንብ መንጋ ከተሞሉ ቀፎዎች ከ1 ሺህ ኪሎ በላይ የማር ምርት ለመሰብሰብ አቅደው እየሰሩ መሆናቸውን የገለፁት ደግሞ በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰከላ ወረዳ ጋፍቲ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ካሳዬ የምድርዓለም ናቸው።
የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ለንብ ማነብ ስራ ተጨባጭ የሆነ የእውቀትና የክህሎት ሽግግር እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።
በክልሉ ባለፈው ዓመት 33 ሺህ ቶን የማር ምርት ተመርቶ ለገበያ ማቅረብ እንደተቻለም ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያመላክታል።