ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ለዘላቂ የምጣኔ ሃብት እድገትና ለብሔራዊ ደህንነቷ መጠበቅ ወሳኝ ነው -ምሁራን

ጎንደር ፤ህዳር 2/2019 (ኢዜአ) ፡-የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ለዘላቂ የምጣኔ ሃብት እድገትና ለብሔራዊ ደህንነቷ መጠበቅ ወሳኝ መሆኑን የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

በአፍሪካ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያላትና ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች የምትገኘው ኢትዮጵያ ህልውናዋን አስጠብቃ ለመዝለቅ አስተማማኝና ዘላቂ የሆነ የባሕር በር ማግኘት እንዳለባት ይታመናል።

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ በዓለም አቀፍ ህግ፣ በመልካአ ምድርም ይሁን በታሪክ ተገቢ የሆነ ጥያቄ በመሆኑ በዲፕሎማሲ ጥረት ምላሽ እንዲያገኝ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።

በመሆኑም በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምሁራን የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ለዘላቂ የምጣኔ ሃብት እድገትና ለብሔራዊ ደህንነቷ መጠበቅ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በዩኒቨርሲቲው የወቅታዊ ጉዳዮች ጥናት አስተባባሪ ሀቢብ ሰኢድ (ረዳት ፕሮፌሰር) የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ በሁሉም መመዘኛዎች ትክክለኛና ተገቢ ጥያቄ መሆኑን አስረድተዋል።

ከ130 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ የባህር በር ተዘግቶባት መኖር የማትችል መሆኑን በማንሳት የህልውና ጉዳይ በመሆኑ የትውልዱ ጥያቄ ምላሽ ማግኘት አለበት ብለዋል።

የባህር በር ከሎጂስቲክስ ሰንሰለት ባለፈ ከሀገር ህልውና ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ሲሆን፣ አሁን ላይ ለትራንዚትና ለወደብ ኪራይ ብቻ በየዓመቱ የሚወጣው ከፍተኛ ወጪ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ክፉኛ እየፈተነው መሆኑን ይናገራሉ ። 

በመሆኑም የባህር በር ባለቤት መሆን የንግድ መስመሮችንና የውጭ ንግድን ከማሳለጡ ባሻገር የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ሰፊ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን ገልጸዋል።

የባህር በር ባለቤት መሆን ከፍተኛ የኢኮኖሚ እና የንግድ ትስስር ፋይዳ እንዳለው አንስተው የውጭ ንግድና ሎጂስቲክስ ማሳለጫ ብቻ ሳይሆን ከሀገር ብሔራዊ ደኅንነት፣ ሉዓላዊነትና ዘላቂ ህልውና ጋር በቀጥታ የሚገናኝ መሆኑንም አስረድተዋል።


 

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት ይበልጣል ዋል (ዶ/ር)፤ በበኩላቸው የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ በተጀመረው ሰላማዊና ህጋዊ አማራጭ ምላሽ እንዲያገኝ መስራት የሁላችንም ሃላፊነት ነው ብለዋል።

በተጨማሪም የባሕር በር ባለቤትነትን ማረጋገጥ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ፣ የህዝብን ደህንነት ለመጠበቅ፣ የኢንዱስትሪ አብዮቱን ለማፋጠንና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎችን አስተማማኝ ለማድረግ ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

በመጨረሻም ባለሙያዎቹ የህግ የበላይነትን በማክበርና ዜጎችን በማስተባበር በዲፕሎማሲያዊና በሰላማዊ መንገድ ሀገራዊ ጥቅምን ማስከበር እንደሚገባ ነው የጠቆሙት።

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት ለመሆን የተጀመረውን የሀገር ህልውና አጀንዳ ለማሳካት ሁሉም በየተሰማራበት መስክ ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም