ቀጥታ፡

የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበር አንድነቷ የተጠበቀና ሉአላዊነቷ የተከበረ ሀገር ለመገንባት ገንቢ ሚና እያበረከተ ይገኛል

አዳማ፣ ህዳር 2/2019 (ኢዜአ)፡-የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበር አንድነቷ የተጠበቀና ሉአላዊነቷ የተከበረ ሀገር ለመገንባት ገንቢ ሚና እያበረከተ መሆኑን የኢፌዴሪ የህገ- መንግስትና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ገለጸ።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የዘንድሮውን 21ኛውን የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን  በዓልን ምክንያት በማድረግ ለትምህርት ተቋማት ያዘጋጀው የአሰልጣኞች ስልጠና መድረክ በአዳማ ተካሂዷል።

በዚህ ወቅት ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢፌዲሪ የህገ-መንግስትና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ሃይለየሱስ ታዬ(ዶ/ር) እንዳሉት፤ የብሄሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበር ህብረ-ብሔራዊነትን ከማጠናከር ባለፈ ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ ወሳኝ ነው።

በተለይም ሀገር ማጽናትና ብልፅግናን ማረጋገጥ የሚቻለው የሀገሪቱን ብዝሃነት በማክበርና የብሄር ብሄረሰቦች ተሳትፎን በማጎልበት መሆኑን ጠቁመዋል።

ለዚህም በዓሉን በማስመልከት የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ በማእከሉና በየደረጃው ባሉት መዋቅሮች አማካኝነት  የሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ አስተምህሮ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው አስገንዝበዋል።

በዓሉ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦችን አብሮነት በሚያጸና መልኩ እየተከበረ መምጣቱን ያወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በበዓሉ አከባበር ሂደትም፣ በፌዴራሊዝም እና በሕገ መንግሥት አስተምህሮ ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር መሰራቱን አስረድተዋል።

ይህም አንድነቷ የተጠበቀና ሉአላዊነቷ የተከበረ ሀገር ለመገንባት ገንቢ ሚና እያበረከተ እንደሚገኝ አንስተዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ያካሄደው የጥናት ግኝትም ይህንን የሚያረጋግጥ እንደሆነ ነው ዋና ዳይሬክተሩ ያመላከቱት።

ዴሞክራሲ እና የፌዴራል ስርዓት ለኢትዮጵያ ህልውና ምሰሶ መሆናቸውን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይህንን በትበብር ማጽናት ያስፈልጋል ብለዋል።

በዚህ ረገድ የህገ- መንግስትና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ንቃተ ህገ መንግስትና ፌዴራላዊ አስተሳሰብ ያዳበረ ማህበረሰብ የመገንባት ተልዕኮውን ለማሳካት ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎች እያደረገ መሆኑን አሳውቀዋል።

ለዚህም ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃንና ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የጀመረውን ስራ በዚህ ዓመትም አጠናክሮ መቀጠሉን አብራርተዋል።

ማእከሉ በፌዴራል ሥርዓትና በህገ መንግስት ዙሪያ በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀራራቢ ግንዛቤ እንዲፈጠር ተልእኮ ወስዶ እየሰራ ስለመሆኑም አክለዋል።

ይህም  ህብረተሰቡ በሀገር ጉዳይ ወጥ የሆነ አቋም  በመያዝ ለአንድነቱና ለዕድገቱ  በጋራ ለመትጋት መነሳሳትን ከመፍጠር አንፃር አበርክቶው የጎላ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል የዜጎች ዋስትና የሆነው ህገ መንግሥት የጸደቀበት  እለት በመሆኑ በየዓመቱ  በልዩ ድምቀት እንደሚከበር ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም