ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ እርምጃን ከኢኮኖሚ ፖሊሲዋ ጋር አስተሳስራ እየሰራች ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ እርምጃን ከኢኮኖሚ ፖሊሲዋ ጋር አስተሳስራ እየሰራች ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ህዳር 2/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ እርምጃን ከኢኮኖሚ ፖሊሲዋ ጋር አቀናጅታ እየሰራች እንደምትገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
31ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በቱርኪዬ አንታሊያ እየተካሄደ ይገኛል።
“ጉዞ ወደ ዘላቂ፣ አይበገሬነት እና ፍትሃዊነት ወደተረጋገጠበት መጻኢ ዘመን” የጉባኤው መሪ ቃል ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ የአየር ንብረት እርምጃን ከኢኮኖሚ ፖሊሲዋ ጋር አስተሳስራ እየሰራች መሆኗን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ኢትዮጵያ በኤልኒኖ ምክንያት የሚከሰተውን ድርቅ እና ጎርፍ የሚያደርሱትን ጉዳት ለመቀነስ ከአካባቢው ማህበረሰቦች ጋር በቅድመ-ማስጠንቀቂያ ላይ ተመስርታ እየሰራች እንደምትገኝ አመልክተዋል።
ከ90 በመቶ በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦቷ ከውሃ የሚመንጭ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህ ንጹህ ኃይል ለጎረቤት ሀገራትም ጭምር የሚቀርብ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የአራቢካ ቡና መገኛ ብትሆንም የአየር ንብረት ለውጥ በቡና እርሻዎች ላይ ደቅኖ የሚገኘውን ስጋት ለመቀነስ የ"መደመር" ፍልስፍናን በመከተል የችግኝ ተከላ እና የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
በታላቁ የአረንጓዴ አሻራ ሀገራዊ እንቅስቃሴ እስከ አሁን ከ56 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውንና ይህም ለዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን ነው የጠቀቆሙት።
በተጨማሪም በአካባቢ ጥበቃ ረገድ ኢትዮጵያ የነዳጅ እና ዲዚል ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ በማድረግ ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች (EV) የመሸጋገር ሀገራዊ እርምጃ መወሰዱን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2027 የሚካሄደውን የኮፕ 32 የአየር ንብረት ጉባኤ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ የምታስተናግድ በመሆኑ፣ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና ልዑካን ወደ ሰው ዘር መገኛ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።