ቀጥታ፡

የ"አፍሪካ ሰለብሪትስ 2026" አህጉራዊ መድረክ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ፤ህዳር 2/2019(ኢዜአ)፦6ኛው ዙር የ"አፍሪካ ሰለብሪትስ 2026" አህጉራዊ መድረክ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት አዳራሽ በይፋ መካሄድ ጀምሯል።

መድረኩ ከህዳር 2 እስከ 5 ቀን 2019 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን “አንድ አፍሪካ፣ አንድ ህዝብ፣ ባህልን፣ ፈጠራና ስራ ፈጠራን ለጋራ ብልጽግና ማዋሃድ” በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ይገኛል።


 

መድረኩን የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከአፍሪካ ህብረት እና ከሌጀንደሪ ጎልድ ሊሚትድ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው።

የመድረኩ ዋና ዓላማ በአህጉሪቱ እና በዳያስፖራው የሚገኙ አፍሪካውያንን በማገናኘት የባህል፣ የቱሪዝም፣ የንግድ እና የኢንቨስትመንት ትስስርን ማጠናከር መሆኑም ተመላክቷል።

በተጨማሪም የአፍሪካን ባህላዊ እሴቶች ከማስተዋወቅ ባለፈ የቴክኖሎጂ እና የስራ ፈጣሪዎችን ከባለሃብቶች ጋር በማገናኘት የዲጂታል ሽግግርን ለማፋጠን ያለመም ነው።

በመድረኩ የተገኙት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሃፍታይ ገብረእግዚአብሔር አዲስ አበባ በኮሪደርና በወንዝ ዳርቻ ልማቶች ተሞክሮ የሚሆን ለውጥ እያስመዘገበች በመሆኑ ለመድረኩ ስኬት ዝግጁ ናት ብለዋል።


 

አዲስ አበባ መድረኩ የታለመለትን ዓላማ ለማሳካት በሚደረገው አህጉራዊ ጥረት የሚጠበቅባትን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መሆኗንም ጠቁመዋል።    

በተጨማሪም የመድረኩ ተሳታፊዎች በከተማዋ የሚገኙ የተለያዩ የልማት ስራዎችንና የአድዋ ድል መታሰቢያን እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም