ቀጥታ፡

በመደመር ፍልስፍናችን እየተመራን የአየር ንብረት ተስማሚ መፍትሄዎችን በስፋት እያሳደግን እንገኛለን - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ  አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ህዳር 2/2019 (ኢዜአ)፦ በመደመር ፍልስፍናችን እየተመራን የአየር ንብረት ተስማሚ መፍትሄዎችን በስፋት እያሳደግን እንገኛለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት የቱርክዬ መንግሥትና ሕዝብ ላደረጉልን ደማቅ አቀባበል፣ እንዲሁም ድርድሩን ለምትመራው አውስትራሊያ የላቀ ምስጋናዬን አቀርባለሁ ብለዋል።

‎ለኢትዮጵያ የአየር ንብረት እርምጃ፤ የዜጎችን የእለት ተእለት ኑሮ ለማሻሻል፣ የመቋቋም አቅምን ለማጠናከር እና የተመዘገቡ የልማት ስኬቶችን ዘላቂ ለማድረግ እጅግ ወሳኝ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲያችን አካል ነው ሲሉም ገልጸዋል።

በመደመር ፍልስፍናችን እየተመራን፣ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብራችን እስካሁን ከ56 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን መትከሉን ገልጸው፤ በተመሳሳይ መልኩ የታዳሽ ኃይል ልማትን፣ ዘላቂ የከተማ ግንባታን እና የአየር ንብረት ተስማሚ መፍትሄዎችን በስፋት እያሳደግን እንገኛለን ብለዋል።

‎አሁን ላይ ከቃል ኪዳን ባለፈ ወደ ፈጣን ተግባራዊ እርምጃዎች መሸጋገር ይኖርብናል ሲሉ ገልጸዋል።

ይህም በቀላሉ ሊገኝ በሚችል የአየር ንብረት ፋይናንስ፣ ይበልጥ ጠንካራ በሆኑ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቶች እና ተጋላጭ ለሆኑ ማህበረሰቦች የመቋቋም አቅም ግንባታ ላይ በሚደረግ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ተግባራዊ መደረግ አለበት ብለዋል።

‎ኢትዮጵያ መጪውን የCOP32 ፕሬዝዳንትነት ስትረከብ እነዚህን ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች በግንባር ቀደምትነት የምታራምድ መሆኑን ገልጸው፤ ስኬታማ ውጤት እንዲመዘገብም ከCOP31 ፕሬዝዳንት ጋር በቅርበትና በትብብር ትሠራለች ብለዋል።

እንዲሁም መላውን ዓለም ለCOP32 ጉባኤ ወደ ምድረ ቀደምት ሀገር ወደሆነችው ኢትዮጵያ ለመቀበል ዝግጁ ነን ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልእክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም