ቀጥታ፡

የመደመር መንግሥት የብዝኅ ኢኮኖሚ ልማት የሴቶችና ወጣቶችን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ነው

አዲስ አበባ፤ህዳር 2/2019(ኢዜአ)፦የመደመር መንግሥት የብዝኅ ኢኮኖሚ የልማት አቅጣጫ የሴቶችና ወጣቶችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያረጋገጠ መሆኑን የክልል የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊዎች ገለጹ።

የመደመር መንግሥት የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ አካታችና አሳታፊ ምኅዳር በመፍጠር ውጤታማ የልማት ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

ለአብነትም በሀገር ውስጥ የብዝኅ ኢኮኖሚ ልማት የዕድገት አቅጣጫን በመከተል የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት እያስገኙ ነው።

በውጭ ሀገራት ሕጋዊ የሥራ ስምሪትም የዜጎች መብትና ክብር ተጠብቆ ጥሪት የሚያፈሩበትን ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓት በመዘርጋት ከፍተኛ ለውጥ ተመዝግቧል።

የክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊዎች ለኢዜአ እንዳሉት፤ የመደመር መንግሥት የብዝኅ ኢኮኖሚ ልማት አቅጣጫ የሴቶችና ወጣቶችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ነው።

ይህም ዜጎች በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጥ አቅም በመገንባት አመርቂ ውጤት እያስገኘ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ የፈጠረችው ሕጋዊ የውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት አስከፊና ሕገ-ወጥ ፍልሰትን በመቀነስ አበረታች ውጤት እያስገኘ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጓዳኝም በሕገ-ወጥ መልኩ ዜጎችን ለከፋ እንግልት የሚያጋልጡ ኤጀንሲዎችንና ደላሎችን በሕግ ቁጥጥር ስር በማዋል ተጠያቂነትን የማስፈን ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ፋጤ ሱርሞሉ እንደሚሉት፤ የመደመር መንግሥት የልማት አቅጣጫ የሥራ ዕድል ፈጠራ አቅምን እያጎለበተ ነው።

ይህም የባለድርሻ አካላትን ትብብር በማጎልበት ዜጎች በሀገራቸው ሰርተው የሚለወጡበትን ዕድል በመፍጠር ሕገ-ወጥ ፍልሰትን እያስቀረ መሆኑን አመላክተዋል።

የማህበረሰብ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባርም በሀገር ውስጥ ሰርቶ የመለወጥ ባህልን በማጎልበትና ሕጋዊ የሥራ ስምሪትን በማበረታታት ሕገ-ወጥነትን እየቀነሰ መምጣቱን አብራርተዋል።

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ምክትል ቢሮ ኃላፊ መርየም አብዱረህማን በበኩላቸው፤ ሕገ-ወጥ ስደት ጉልህ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ያስከትላል ብለዋል።

የሕገ-ወጥ ፍልሰት አስከፊነትን በተመለከተም ተከታታይ የማህበረሰብ ግንዛቤ ማስጨበጫ በመስራት ዜጎች በሀገራቸው ሰርተው እንዲለወጡና ሕጋዊ የሥራ ስምሪትን እንዲጠቀሙ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በሕጋዊ የሥራ ስምሪት እና ከሕገ-ወጥ ስደት የተመለሱ ሴቶችንና ወጣቶችን በሀገራቸው ሰርተው የሚለወጡበትን ዕድል በመፍጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

የመደመር መንግሥት ዘመናዊ የውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት ምኅዳር ፈጥሯል ያሉት ደግሞ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ራሔል ሌዊ ናቸው።

በዚህም ወደ ውጭ ሀገራት ለሥራ ስምሪት የሚጓዙ ዜጎች መብትና ክብራቸው ተጠብቆ የሚሰሩበትን ዘመናዊና የተደራጀ ሥርዓት በመገንባት እየተሰራበት መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም