የኢትዮጵያ መንግሥት የሴቶችና ወጣቶች ውሳኔ ሰጭነትን ለማጎልበት የፈጠረው የፖለቲካ ምኅዳር ትልቅ ምሳሌ የሚሆን ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መንግሥት የሴቶችና ወጣቶች ውሳኔ ሰጭነትን ለማጎልበት የፈጠረው የፖለቲካ ምኅዳር ትልቅ ምሳሌ የሚሆን ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 2/2019 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ መንግሥት የሴቶችና ወጣቶች ውሳኔ ሰጭነትን ለማጎልበት የፈጠረው አካታች የፖለቲካ ምኅዳር ለሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ትልቅ ምሳሌ የሚሆን ነው ሲሉ በአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ ላይ የተሳተፉ ወጣቶች ገለጹ።
2ኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ "ዕድገትን መምራት ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ የአፍሪካ መጻኢ ኢኮኖሚ መሃንዲሶች" በሚል መሪ ሀሳብ ከጥቅምት 26 እስከ 28/2019 ዓ.ም ተካሂዷል።
በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ በተካሄደው ጉባዔ፣ ከ54 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ 1 ሺህ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ ባለድርሻ አካላትና ተጋባዥ እንግዶች ተሳትፈዋል።
የጉባዔው ተሳታፊ ወጣቶች ለኢዜአ እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው የልማት ተሞክሮ የሚደነቅ እና የሴቶችና የወጣቶች ተሳትፎ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ትምህርት የሚሰጥ ነው።
ከካሜሩን የመጣችው ወጣት ንጋኮ ፓትሪሺያ ቴልሲ ሞቬኒ፣ በኢትዮጵያ ሴቶችና ወጣቶች በአመራር ሰጪነት ያላቸው ተሳትፎ የሚደነቅና ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት አርዓያ የሆነ ነው ብላለች።
በጉባዔው ላይ ሴቶችና ወጣቶች በመሳተፍ ስለአፍሪካ መፃኢ ዕድል በጋራ መምከራቸው የሚደነቅ ብሎም ለአህጉሪቱ ልማት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግራለች።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ መዲናና የአህጉሪቱን የወደፊት ዕድል በመቅረጽ በኩል ጠቃሚ ሥፍራ እንዳላት ገልጻለች።
በኢትዮጵያ ሴቶችና ወጣቶችን በውሳኔ ሰጪነት ተሳትፎ ያላቸው መሆኑ ለኢትዮጵያ ሊያበረክቱ የሚችሉት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን አመልክታለች።
ሌላው አስተያየት ሰጪ ከሞሮኮ የመጣው ሊማም ቡሲፍ በበኩሉ፣ የኢትዮጵያ የልማት ስኬቶች አስገራሚ መሆኑን አንስቷል።
አፍሪካን በተፈጥሮ ሀብት የታደለች የወጣት አህጉር በመሆኗ አቅሟን በመጠቀም ለመጪው ትውልድ የተሻለ ነገ መገንባት እንደሚገባ ተናግሯል።
ወጣቶችና ሴቶች ከምርጫ ተሳትፎ ባለፈ በውሳኔ ሰጪነት ደረጃ እንዲሳተፉ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስገንዝቧል።
ከኡጋንዳ የመጣችው አኩዊ ኖራ ሮቢና በበኩሏ የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ልማት ለሌሎች ሀገራት በአርዓያነት የሚጠቀስ መሆኑንና የእንግዳ አቀባበሉም ቤታቸው እንዳሉ እንዲሰማቸው ያደረገ መሆኑን ተናግራለች።
የኢትዮጵያ መንግሥት የሴቶችን የውሳኔ ሰጪነት ለማጎልበት ያከናወነችው ተግባር የሚደነቅ መሆኑን አንስታ፤ ሌሎች ሀገራትም በስርዓተ ፆታ እኩልነት ላይ እንደኢትዮጵያ ካሉ ሀገራት ትምህርት ሊቀስሙ ይገባል ብላለች።