ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በወጣቶች ኦሊምፒክ በአትሌቲክስ አንደኛ ደረጃን ይዛ አጠናቀቀች

አዲስ አበባ፤ ህዳር 2/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በሴኔጋል እየተካሄደ በሚገኘው አራተኛው የወጣቶች ኦሊምፒክ ጨዋታዎች በአትሌቲክስ አንደኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

በወጣቶች ኦሊምፒክ የአትሌቲክስ ውድድር ዛሬ ፍጻሜውን አግኝቷል።

በዚህም ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ 5 የወርቅና 3 የብር ሜዳሊያዎችን፣ በድምሩ 8 ሜዳሊያዎችን በማሸነፍ በዓለም የአትሌቲክስ ሜዳሊያ ሰንጠረዥ አንደኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቅቃለች።

ይህ ውጤት የኢትዮጵያን የአትሌቲክስ ታሪክ የሚያስቀጥሉ ተተኪ ወጣት አትሌቶች ብቃትና የወደፊት ተስፋ የሚያሳይ ታላቅ ስኬት መሆኑን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያ በወጣቶች ኦሊምፒክ ከአትሌቲክስ በተጨማሪ በብስክሌት፣ ቴኳንዶ፣ ውሹ እና ውሃ ዋና ስፖርቶች ተሳትፋለች።

በውሹ ታዳጊው ናትናኤል ክንፈ የነሐስ ሜዳልያ አግኝቷል።

ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ስፖርቶች አምስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ቻይና፣ ጃፓን፣ ሩሲያ እና ግብጽ በሜዳሊያ ሰንጠረዡ ከአንደኛ እስከ አራተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

የወጣቶች ኦሊምፒክ በ25 የስፖርት ውድድር አይነቶች ሲካሄድ ቆይቷል።

ጥቅምት 21 2019 ዓ.ም የተጀመረው አራተኛው የወጣቶች ኦሊምፒክ ሻምፒዮና ሕዳር 4 2019 ዓ.ም ፍጻሜውን ያገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም