የኢትዮጵያ ድል፦ የጀግኖች አሻራ በዓለም አደባባይ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ድል፦ የጀግኖች አሻራ በዓለም አደባባይ
የኢትዮጵያ አትሌቶች በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የሚያስመዘግቡት ድል ከሜዳሊያ ባለፈ ጥልቅ የሆነ ብሔራዊ ትርጉም አለው። ይህ ድል የሕዝብን አንድነት የሚያጠናክር፣ የታሪክን ትስስርን የሚያድስ እና የነፃነት አርማ ሆኖ የሚያገለግል የጀግንነት መግለጫ ነው።
አትሌቶች የፍጻሜዋን መስመር አልፈው ድል ሲያደርጉ እና የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ ሲሰቀል፣ በኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈጥረው የደስታ ስሜት ስፖርታዊ ድል ብቻ ሳይሆን የሀገር ፍቅር፣ የጽናት እና የማንነት ማረጋገጫ ታላቅ ብሔራዊ አሻራ ነው።
የኢትዮጵያ አትሌቶች ይህንን የጀግንነት እና የጽናት ታሪክ ከትውልድ ወደ ትውልድ በማሻገር ረገድ ግንባር ቀደም ሚና አላቸው።
አበበ ቢቂላ በሮም በኦሊምፒክ በባዶ እግሩ ሮጦ ወርቅ ሲያጠልቅ፣ የአፍሪካውያንን ክብርና አሸናፊነት ለዓለም ያበሰረበት ታሪካዊ ክስተት ሁሌም የሚታወስ ነው።
ይህንን የድል ችቦ የተረከቡት እንደ ኃይሌ ገብረሥላሴ እና ቀነኒሳ በቀለ ያሉ አትሌቶች በጽናታቸውና በማይበገረው ወኔያቸው የኢትዮጵያን ስም በዓለም አደባባይ ከፍ አድርገውታል።
እነዚህ ጀግኖች የመሮጫ ትራክ ላይ ሲያሸንፉ የሀገርን ህዝብ ኩራት እና የቁርጠኝነት መንፈስ አብረው አንግበው ነው።
በሴቶች በኩል የተመዘገቡት ድሎችም የሀገርን ስም ከማስጠራት ባለፈ የሴቶችን ብቃት እና ጥንካሬ ለአለም ያሳዩና ታሪክ የሰሩ አትሌቶች ሀገር ናት ኢትዮጵያ።
ከነዚህም መካከል ደራርቱ ቱሉ በባርሴሎና በኦሊምፒክ ያስመዘገበችው ታሪካዊ ድል የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአጠቃላይ አፍሪካውያን ሴቶች የመጀመሪያው የኦሊምፒክ ወርቅና የኩራት ምንጭ ሆኗል።
ይህንን ፈለግ በመከተል ፋጡማ ሮባ በማራቶን፣ እንዲሁም ጥሩነሽ ዲባባ እና መሰረት ደፋር በረጅም ርቀት ሀገራቸውን በታላላቅ መድረኮች ላይ ደጋግመው ሲያሸንፉ፣ የሀገር ፍቅር ስሜት እና የወገን ኩራት በውስጣቸው እንዴት እንደሚቀጣጠል በተግባር አሳይተዋል።
ከግል ጀግንነት ባለፈ፣ የአትሌቶቻችን መለያ የሆነውና በዓለም አደባባይ «አረንጓዴው ጎርፍ» እየተባለ የሚጠራው የቡድን ስራ፣ ጠንካራ የኅብረትና የአንድነት ተምሳሌት ነው።
ይህ የአትሌቶች ሜዳ ላይ በአንድነት ተደጋግፎና ተጋግዞ የመውጣት ስነ-ህብረት፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በነቂስ ወጥተው በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን ከተከሉበት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ጋር ቀጥተኛ ትስስር አለው።
ሁለቱም ጉዳዮች የሚያስተላልፉት አንድ ግልጽ መልዕክት አለ። ኢትዮጵያውያን በአንድ ልብ ሲሰለፉ ሊመዘገብ የሚችለውን ታላቅ ሀገራዊ ስኬት እና አሻራን ያሳያሉ።
ከድሮ እስከ አሁን የተፈራረቁት የኢትዮጵያ አትሌቶች በደምና በላባቸው የጻፉት ታሪክ የጀግንነት ህያው ምስክር ነው።
የእነሱ አሸናፊነት በዓለም መድረክ ላይ ሀገርን ከማስጠራት ባለፈ፣ ልክ በአረንጓዴ አሻራ ላይ እንደሚታየው ህዝባዊ መነሳሳት፣ ለቀጣዩ ትውልድ የማይቻል ነገር የለም የሚል የጽናትና የአንድነት ትምህርት ጥሎ ያልፋል።
አትሌቶች በሮጡና በአንድነት ሲሮጡ የሚያንጸባርቁት የሀገር ፍቅር ስሜት፣ ኢትዮጵያ ሁልጊዜም በነፃነት፣ በአረንጓዴነት እና በአሸናፊነት ከፍ ብላ እንድትኖር የሚያደርግ ብሔራዊ ኩራቷ ነው።